በህንድ የተከሰተው የጥቁር ፈንገስ በሽታ በወረርሺኝነት እንዲታወጅ ጥሪ ቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በህንድ የሚገኙ ክልሎች ‹‹የጥቁር ፈንገስ›› አማካኝነት የሚከሰተው በሽታ በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በወረርሺኝነት እንዲታወጅ የአገሪቱ የጤና ሃላፊዎች ጠየቁ።
ከዚህ ቀደም እንብዛም የማይታየው እና በዚህ ፈንገስ አማካኝነት የሚከሰተው የሚውኮርማይኮሲስ በሽታ እስከ 50 በመቶ ድረስ ገዳይ ሲሆን የሚተርፉ ሰዎችም አይናቸውን ወይም የመንጋጋ አጥንት ያጣሉ።
ከቅርብ ወራት ጀምሮ ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ከ ኮቪድ ያገገሙ እና በማገገም ላይ ያሉ ሰዎች በሚውኮርማይኮሲስ ተይዘው ተገኝተዋል።
የኮቪድ ህመምተኞችን ለማከም ከዋሉ መድሃኒቶች ጋር ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል ሃኪሞች ጥርጣሬያቸውን ገልፀዋል።
በተለይም የስኳር ህመምተኞች ከኮሮና ቫይረስ ነፃ ከሆኑ ከ 12 እስከ 15 ባሉት ቀናት ውስጥ ተጋላጭ ሳይሆኑ እንዳልቀረ ሃኪሞቹ ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የህንድ የጤና ሚኒስትር የጽህፈት ቤት ሃላፊ ላቭ አጋርዋል በህንድ ላሉ 29 ክልሎች ይህንን ህመም ወረርሺኝ ብለው እንዲያወጁ በደብዳቤ ጠይቀዋል።
ህመሙ ወረረሺኝ ተብሎ የሚታወጅ ከሆነ ከጤና ሚኒስቴር የተሸለ ትብብር አና ህክምና ለመስጠት ብሎም በእያንዳንዱ ክልል ያለውን ሁኔታ ለመከታተል ያስችላል ተብሏል።
በኮሮና ቫይረስ እየተናጠች ባለችው ህንድ እስካሁን ድረስ ምን ያህል ሰዎች በሚውኮርማይኮሲስ እንደተያዙ በውል አይታወቅም።
በህንድ ባጋጠመው ሁለተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ የስርጭት ማእበል በሁለተኛ ደረጃ ተጠቂ የሆነችው ማሃራሽትራ ክልል እስካሁን 1500 የሙኮርሚኮሲስ ታማሚዎችን ለይታለች።
በህንድ ዋና ከተማ ሙምባይ የሚገኝ አንድ ሆስፒታል በሁለት ወር ውስጥ 24 ህመምተኞችን መመልከቱ እና ይህ ባለፈው አመት ከታየው ስድስት ህመምተኛ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።
ሃኪሞችም ፈንገሱ ወደ አእምሮ ሳይሰራጭ የህመምተኞችን ህይወት ለማትረፍ የመንጋጋ አጥንትን ወይም አይናቸውን ለማስወገድ መገደዳቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በበርካታ የህንድ የመድሃኒት አምራቾች የሚመረተው እና ይህንን ህመም ለማከም የሚለው አምፎተሪሰን የተሰኘው መድሃኒት እጥረት መከሰቱም ታውቋል።












