ማላዊ በሺዎች የሚቆጠሩ የኮቪድ-19 ክትባቶችን አስወገደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የማላዊ የጤና ባለሥልጣናት 19,610 የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን የአስትራዜኔካ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባትን አስወገዱ።
እርምጃው ሕብረተሰቡ የሚያገኘው ክትባት ለአደጋ የማያጋልጥ ስለመሆኑ ያረጋግጣል ተብሏል።
ማላዊ ይህንን በይፋ ያከናወነች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አገር ነች።
የዓለም ጤና ድርጅት ቀደም ሲል አራት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ክትባቶች እንዳያስወግዱ አጥብቆ ቢያሳስብም በኋላ ላይ ሃሳቡን ቀይሯል።
በማላዊ ክትባቱን የሚውሰዱ ሰዎች ቁጥር በጣም ዝቅተኛ የነበረ ሲሆን እርምጃው የሕዝቡን እምነት እንደሚያሳድገው የጤና ባለሙያዎች ተስፋ አድርገዋል።
ወደ 18 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት አገሪቱ 34,232 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሲያዙባት የ1153 ሰዎችን ህይወት በወረርሽኙ ተነጥቃለች።
ማላዊ ከአፍሪካ ሕብረት 102,000 ብልቃጥ የአስትራዜኔካ ክትባት ተቀብላ 80 በመቶ የሚሆነውን ተጠቅማለች።
የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ክትባቶች በመለየትም ከስርጭት እንዲወጡ ተደርገዋል።
የማላዊ የጤና ዋና ኃላፊ ለቢቢሲ እንደገለፁት ክትባቶቹን ማውደማቸው አሳዛኝ ቢሆንም ጥቅሙ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች ይበልጣል።
ዶ/ር ቻርለስ ምዋንሳምቦ በበኩላቸው "ጊዜ ያለፈበት ክትባት ስለመያዛችን መረጃው ሲሰራጭ ሰዎች ወደ ክሊኒካችን ከመምጣት እንደተቆጠቡ አስተውለናል" ብለዋል።
"ካላስወገድናቸው በእኛ ተቋማት ውስጥ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ክትባቶችን እንደምንጠቀም ካሰቡ ሰዎች ስለሚቀሩ በኮቪድ-19 በጣም ይጎዳሉ።"
የማላዊ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ኩምቢዜ ቺፒንዳ ረቡዕ እለት ጊዜ ያለፈባቸው ክትባቶች የማቃጠያ ክፍሉን ሲዘጉ ፎቶግራፍ ተነስተዋል።
በዋና ከተማው ሊሎንዌ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች የክትባቱ ደኅንነት ጉዳይ አስጨንቋቸዋል።
"መከተብ ብፈልግም ወደ ሆስፒታል ከሄድኩ ጊዜው ያለፈበት ክትባት እንዳልተሰጠኝ ምን ያህል እርግጠኛ እሆናለሁ?" ሲል በመንግሥት ሥራ የተሰማራው ጃክ ቺቴቴ ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ሰዎች የደም መርጋት እንዳጋጠማቸው እና አንዳንዶችም ከተከተቡ በኋላ ስለሚሞታቸው ሰምቻለሁ። እነዚያ ሰዎች ውሸትን እየናገሩ ነውን? እውነት ከሆነ ለምን ተመሳሳይ ክትባቶች ይሰጡናል?" በማለት ሌላኛው ነጋዴ ምፋሶ ቺፔንዳ ጠይቋል።
በአስትራዛኔካ ክትባት እና አልፎ አልፎ በሚያጋጥመው የደም መርጋት መካከል ያለው ትስስር ያልተረጋገጠ ሲሆን የመከሰት እድሉም ኮቪድ -19 ካለው ስጋት አንጻር አነስተኛ በመሆኑ ሰዎች ከቻሉ ክትባት እንዲወስዱ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።
በአፍሪካ ውስጥ ጊዜው ያለፈባቸው ክትባቶችን የያዘችው ማላዊ ብቻ አይደለችም። የዓለም ጤና ድርጅት መጀመሪያ ላይ በድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል አለመቻላቸውን እስኪያረጋግጥ ድረስ ክትባቱን እንዲይዙ ጠየቆ ነበር።
አሁን ግን በአምራቹ መጠቀሚያ ጊዜ ተጽፎባቸው ተመርተው ጊዜው ያለፈባቸው ክትባቶች መወገድ አለባቸው ብሏል።
"ክትባቶችን ሳይጠቀሙ ማስወገድ ከክትባት መርሃ ግብር አንፃር የሚያሳዝን ቢሆንም፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ክትባቶች ከስርጭት ሰንሰለቱ ወጥተው በጥንቃቄ ይወገዱ" ሲል የዓለም የጤና ድርጅት መክሯል።
በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት ላይ እየዋሉ የሚገኙ ሌሎች ክትባቶች እስከ 36 ወር ድረስ ጥቅም ላይ የመዋያ ጊዜ አላቸው።
የኮቪድ-19 ክትባቶች አገልግሎት ላይ መዋል ከጀመሩ ከአንድ ዓመት በታች የሆነ ጊዜ ብቻ ስለሆናቸው ከረጅም ጊዜ በኋላ ስለሚኖራቸው ውጤታማነት ተጨባጭ መረጃ አለመኖሩ ዋነኛው ተግዳሮት ነው ተብሏል።













