ኮሮናቫይረስ: የአፍሪካ ሃገራት ለምን የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን ያባክናሉ?

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
ምንም እንኳን በርካታ የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ከፍተና ትግል እያደረጉ ቢሆንም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ክትባቶች ግን የመጠቀሚያ ጊዘያቸው እያለፈ እየተጣሉ ነው።
ማላዊ እስካሁን ድረስ 16 ሺ 400 የኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ እንዲሁም ደቡብ ሱዳን ደግሞ 59 ሺ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ክትባቶች እንደሚገኙ ተገልጿል። የክትባቶቹ የመጠቀሚያ ጊዜ ደግሞ ከሁለት ሳምንታት በላይ አልፎበታል።
ሁለቱም አገራት በአፍሪካ ሕብረት በኩል ያገኙትና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈውን ክትባቶች ለማስወገድ የወሰኑ ቢሆንም የዓለም ጤና ድርጅት ግን ጉዳዩን እስከማጣራና ምናልባት የመጠቀሚያ ጊዜውን ማራዘም የሚቻልበትን መንገድ እስከምፈልግ አታስወግዱ በማለት ጠይቋል።
በሌላ በኩል ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደግሞ ለድሀ አገራት ክትባቶችን በሚያከፋፍለው ኮቫክስ በኩል ካገኘችው 1.7 ሚሊየን የአስትራዜኔካ ክትባቶች ውስጥ አብዛኛውን እንደማትጠቀመው አስታውቃለች።
በአገሪቱም እስካሳለፍነው ወር መጨረሻ ድረስ 1 ሺ ክትባቶች ብቻ ናቸው ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት።
በተጨማሪ ደግሞ በሚቀጥለው ወር የመጠቀሚያ ጊዜያቸው የሚያልፍባቸው ክትባቶች ወደ ቶጎ እና ጋና ይላካሉ ተብሎ ይጠበቃል። እነዚህ አገራት መጀመሪያ ላይ የተላከላቸውን ክትባቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ አውለዋል ተብሏል።
የኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ ምርት የሆነው ክትባት በአግባቡ ከተቀመጠና በተገቢው የቅዝቃዜ መጠን ደህንነቱ ከተጠበቀ ከምርት በኋላ እስከ ስድስት ወራት ድረስ ሳይበላሽ መቆየት ይችላል።
አሁን ላይ ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት የካቲት ወር ላይ ደቡብ አፍሪካ ተልከው የነበሩ ክትባቶችን መልሶ ወደ ሌሎች አገራት ማከፋፈል ጀምሯል። ደቡብ አፍሪካ የአስትራዜኔካ ክትባት አሁን ያለውን አዲስ የቫይረስ አይነት በበቂ ሁኔታ መከላከል ስለማይችል አልጠቀመውም ብላለች።
ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ የአፍሪካ ሕብረት ለአባል አገራት እንዲያከፋፍም ተብሎ አንድ ሚሊየን ክትባቶችን ገዝቷል። ነገር ግን እንደ ደቡብ ሱዳን ያሉ አገራት ክትባቱ የመጠቀሚያ ጊዜው መቼ እንደሚያልፍ አልተነገረንም ብለዋል።
ናይጄሪያ ደግሞ ክትባቶቹ ወደ አገሪቱ ቢገቡ እንኳን የመጠቀሚያ ጊዜው ከማለፉ በፊት ጥቅም ላይ ማዋል እንደማትችል ገልጻለች። ይህን ተከትሎ ክትባቶቹ እንደ ቶጎ እና ጋና ወደመሳሰሉ ሌሎች አገራት እንዲሰራጩ እየተደረገ ነው።
ቀሪዎቹ ክትባቶች ደግሞ ወደ ጃማይካ ጭምር እንዲላኩ ተደርጓል።
የዓለም ጤና ድርጅት፤ የክትባቱ የመጠቀሚያ ጊዜ ሳያልፍ በአግባቡ ዜጎቻቸውን የከተቡት ቶጎ እና ጋምቢያ ብቻ ናቸው ብሏል። በሌሎቹ አገራት ደግሞ በትክክል ክትባቱ ስለመዋል አለመዋሉ በቂ መረጃ አልተገኘም።
በርካታ አገራት ክትባቶቹን በአግባቡ ጥቅም ላይ እያዋሉ ያልሆነው በበቂ ሁኔታ ክትባቱን ለማስቀመጥና ለማቆየት በቂ ዝግጅት አለማድረጋቸው መሆኑን ይገልጻሉ የዓለም ጤና ድርጅት አፍሪካ ውስጥ የሚሰሩት ፒዮናህ አቱሄብዌ።
‘’በአሁኑ ሰአት ክትባቱን በፍጥነት እንዳናዳርስ የያዘን ዋነኛው ምክንያት ይሄ ነው’’ ይላሉ።
ሌሎች አገራት ደግሞ የገንዘብ ችግር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠር ማዕከል ኃላፊው ጆን ንኬንጋሶንግ እንደሚሉት የአፍሪካ አገራት የጤና ባለሙያዎችን ቁጥር በመጨመርና ለእነሱ የሚሆን እንደ ማስክና መሰል መከላከያዎችን በማዘገጀት የክትባቱን ሂደት ማፍጠን ይችላሉ።
ከዚህ በተጨማሪ አገራት ያከማቹት ክትባት የመጠቀሚያ ጊዘው ለማለፍ ከተቃረበ አልያም የመጠቀሚያ ጊዜው ካለፈ የዓለም ጤና ድርጅትን አልያም ሲዲሲን ማነጋገር አለባቸው ይላሉ።
‘’አፍሪካ እንደ አህጉር ክትባት እንዴት መሰጠት እንዳለበት ታውቃለች፤ ከዚህ በፊትም የብዙ በሽታዎች ክትባቶች ተሰጥተው ያውቃሉ’’ ብለዋል ኃላፊው።
‘’ነገር ግን ዋናው ጥያቄ ይህንን ልምዳችን እንዴት እንጠቀምበት ነው? . . . . ፍጥነት በተሞላበት መልኩ’’
ለዴሞክራቲክ ኮንጎ ዋነኛው ችግር ደካማ የጤና አገልግሎት መኖሩ ብቻ አይደለም፤ አገሪቱ ያላት ደካማ የመሰረት ልማትም ነገሮችን ከባድ አድርጓል። በዚህ ምክንያት ክትባቶቹን በተፈለገው ሰአትና ቦታ ማድረስ በጣም አስቸጋሪ ነው።
ነገሮችን ይበልጥ አስቸጋሪ ያደረገው ደግሞ አገሪቱ ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ የአስትራዜኔካ ክትባት ከደህንነት ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ እንዳይውል ማገዷ ነበር። ነገር ግን በቀጣዩ ወር አጋማሽ ላይ ክትባቱ በድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቅዳለች።
ማላዊ ውስጥ የተላላፊ ቫይረሶች ባለሙያ የሆኑት ጋማ ባንድዌም እንደሚሉት ክትባቶቹን ያለማመን አባዜ ክትባቶቹ በተቻለ ፍጥነት ለሚፈልጉ ሰዎች እንዳይደርሱ አድርጓል።
ደብ አፍሪካ ከደም መርጋትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የአስትራዜኔካ ክትባትን አልጠቀምም ማለቷ ደግሞ ሌሎች አገራትም ክትባቱን እንዳያምኑት አድርጓቸዋል።
የአፍሪካ ሲዲሲ ክትባቱን ሊቀበሉ በነበሩ 15 አገራት ባሰራው አንድ ጥናት መሰረት ደግሞ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሰዎች ክትባቱን ለመውሰድ ስጋት ያለባቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ ከነጭራሹ መውሰድ አይፈልጉም።
በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል በአማካይ 20 በመቶ የሚሆኑት ክትባቱን መወጋት አንፈልግም ብለዋል። ነገር ግን በእያንዳንዱ አገር የነበረው ፍላጎት የተለያየ ነው።
ለምሳሌ በኢትዮጵያ፣ ቱኒዚያ እና ኒጀር ክትባቱን መውሰድ አንፈልግም ያሉት ሰዎች 10 በመቶ ሲሆኑ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ደግሞ 41 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች መከተብ አንፈልግም ብለዋል።













