በካሪቢያን ደሴት የተከሰተው እሳተ ገሞራ 'አመድ አዘነበ'

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በካሪቢያን በቅዱስ ቪንሰንት ደሴት የተከሰተው እሳተ ገሞራ የፈጠረው ከፍተኛ የዓመድ ብናኝ ደሴቲቱን አጥለቅልቋል። ይህም ነዋሪዎቿ ላይ ከፍተኛ መደናገጥን ፈጥሯል።
ርዕሰ ከተማዋን ኪንግስታውንን ጨምሮ በደሴቲቱ የሚገኙ ህንፃዎችና መንገዶች ነጭ ቀለም ባለው ብናኝ ተሸፍነዋል።
'ላ ሶፍሪየር' የሚል ስያሜ የተጠው እሳተ ገሞራ ያስከተለው ከፍተኛ የአመድ ብናኝ ቅዳሜ'ለት በሽዎች የሚቆጠር ሜትሮችን በአየር ላይ ሸፍኖ ተስተውሏል። እናም የደሴቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ህዝባቸውን ተረጋጉ ብለዋል።
ለአስር ዓመታት 'በዝምታ' የቆየው
እሳተ ገሞራ ባለፈው ታህሳስ ወር ግን ሀይሉን ማሳየትና ጉዳት ማድረስ ጀመረ።
በዚህም ምክንያት ሺዎች ከቤት ንብረታቸው ለመፈናቀል የተገደዱ ሲሆን የደሴቷ አብዛኛው ክፍል የውሃ አቅርቦት ተቋርጧል።
ወደ 3ሺህ የሚጠጉ ሰዎች አርብ ምሽት በአደጋ ጊዜ መጠለያዎች እንዳሳለፉና 16 ሺህ ሰዎች በብናኙ በተወጡና ለአደጋ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች መፈናቀላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ራንስትር
ራልፍ ጉንሳልቪስ ገልፀዋል። እሳተ ገሞራው ከዚህ በኃላ ምን ያህል የአመድ ብናኝ እንደሚፈጥር አይታወቅምም ያሉ ሲሆን የዘርፉ ጠበብቶች ደግሞ የእሳተ ገሞራው ለቀናት ከፋ ሲልም ለሳምንት ሊቀጥል ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
110 ሺህ አካባቢ የሚሆኑት የደሴቷ ነዋሪዎች ያለፍው ቅዳሜ ማለዳ ላይ ቤቶቻቸው በነጭ የአመድ ብናኝ ተሸፍኖ ነው የነቁት።
የአመዱ ብናኝ ከቅዱስ ቪንሰንት ደሴት ባሻገር 100 ማይሎችን ርቆ ባርዳቦስ ደሴት ላይም ድርሷል። የደሴቷ ባለስልጣን ነዋሪዎች በቤት እንዲቆዩ አሳስበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ዛሬ [ዕሁድ] በደሴቷ ተጨማሪ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ተከስቶ በበርካታ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ሀይል እንዲቋረጥ ምክንያት መሆኑን የሀገሪቱ የአደጋ መከላከል መስሪያ ቤት አስታውቋል።












