ታዋቂው ግሪካዊ የወንጀል ዘጋቢ በጥይት ተገደለ

ጊዮርጊስ ካራይቫዝ

የፎቶው ባለመብት, Xamos

ታዋቂው ግሪካዊ የወንጀል ዘጋቢ በተተኮሰበት ጥይት መገደሉን ተከትሎ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪይራኮስ ሚትሶታክሲ ፈጣን የሆነ ምርመራ እንዲከፈት አዘዋል።

ጊዮርጊስ ካራይቫዝ የተባለው ጋዜጠኛ የተገደለው በያዝነው ሳምነት አርብ በዋና ከተማዋ አቴንስ ከሚገኘው ቤቱ አቅራቢያ ነው።

ሁለት ግለሰቦች ቢያንስ ስድስት ጊዜ ተኩሰው እንደገደሉትም ተዘግቧል።

ሞቱ " ሁላችንንም ድንጋጤ ውስጥ ከቶናል" በማለት የመንግሥት ቃለ አቀባይ ተናግረዋል።

በሚዲያ ነፃነት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች በበኩላቸው ጊዮርጊስ የተገደለበት ምክንያት ከስራው ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ሊጣራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጊዮርጊስ የተደራጁ ወንጀሎችንና ሙስናን በማጋለጥ ዝናን አትርፏል።

ጋዜጠኛው የግል ለሆነው ስታር ቴሌቪዥን እንዲሁም ብሎኮ ለተባለ ድረ ገፅ ይሰራ ነበር። ከስራ ተመልሶ ቤቱ አካባቢ ሲደርስ ከመኪናው በወጣበት ቅፅበት እንደተተኮሰበትም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የአይን እማኞች ነገሩኝ ብሎ ዘግቧል።

የተገደለበት አካባቢም በርካታ የሽጉጥ ቀለሃዎች መሰብሰባቸውን ከፖሊስ ምንጮች መረዳት ተችሏል።

"ጋዜጠኛው የተገደለው በአልሞ ተኳሾች ነው" በማለት ስሜ አይጠቀስ ያለ ፖሊስ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግሯል።

ከግድያው በፊት "ጊዮርጊስ ማስፈራሪያ ደርሶኛል አላለም እንዲሁም የፖሊስ ጥበቃም ያስፈልገኛል አለማለቱን" አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባበው አስነብቧል።

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ቮን ደር ሊየን በእንዲህ አይነት አሰቃቂና አሳዛኝ ሁኔታ መገደሉን በማውገዝ ፍትህ ይገባዋል ብለዋል።

የአውሮፓ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ዴቪድ ሳሶሊ በኩላቸው የጋዜጠኛውን ሞት "አሳዛኝ ነው" በማለት በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

በአውሮፖ ህብረት አባል አገራት ከዚህ በፊት የተገደለው ጃን ኩኪያክ የተባለው ጋዜጠኛ ከሶስት አመት በፊት ነበር። የስሎቫኪያ ዜግነት ያለው ይህ ጋዜጠኛ ግድያ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።