በኖርዌይ ከሞቱ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ በቤታቸው የተገኙት ግለሰብ አስከሬን ጥያቄ አስነሳ

በኖርዌይ ከሞቱ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው አስከሬናቸው የተገኘው ግለሰብ ጉዳይ ፖሊስ ጥያቄ እንዳጫረበት ከሰሞኑ አስታውቋል።
በ60ዎቹ እድሜ ላይ የሚገኙት ግለሰብ ከሞቱ ዘጠኝ ዓመታትን ቢያስቆጥሩም መሞታቸው ሳይታወቅ እስካሁን ቆይቷል ተብሏል።
ፖሊስ ለኖርዌይ ሚዲያ ኤንአርኬ እንደተናገረው ግለሰቡ ጠፍተዋል ወይም ለዚህን ያህል ዓመታት አልታዩም ብሎ ሪፖርት ያደረገ አካል እንደሌለ ነው።
ፖሊስ የግለሰቡን አስከሬን ያገኘው በዋናዋ መዲና ኦስሎ በሚገኝ የጋራ መኖሪያ ቤት በባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር ውስጥ ነው።
እንደ ኤንአርኬ ዘገባ ከሆነ የግለሰቡ አስከሬን የተገኘው ህንፃውን የሚቆጣጠረው ግለሰብ አንዳንድ ጥገናዎች ለመስራት ወደ መኖሪያ ቤታቸው በመግባቱ ነው።
ፖሊስ በስፍራው ላይ የተገኙ የወተት ካርቶኖችን፣ ደብዳቤዎችንና ሌሎች መረጃዎችን በማጣቀስ ግለሰቡ የሞቱት በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2011 መሆኑን ነው።
የኦስሎ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ኃላፊ ግሬት ሊየን ሜትሊድ ለኤንአርኬ እንደተናገሩት "ለዓመታት በተለያዩ ሞቶች ላይ የሰራነው እኔም ሆነ የሥራ ባልደረቦቼ በጣም ነው ያሳሰበን" የሚሉት ኃላፊው "ይሄ ለየት ያለ ጉዳይ ነው፤ እንዴት ለዚህን አመታት ያህል መሞታቸው ሳይታወቅ ቆየ የሚለው በርካታ ጥያቄዎችን የሚያጭር ነው" በማለት ያክላሉ።
አስከሬኑ ላይ በተደረገ ምርመራ ግለሰቡ በተፈጥሯዊ ምክንያቶች መሞታቸውን ጠቁሟል።
የኖርዌይ የሥራና ደኅንነት አስተዳደር የጡረታ ገንዘባቸውን መላክ ያቆመው ከሦስት ዓመታት በፊት ነው። መስሪያ ቤቱ ግለሰቡን ማግኘት ስላልቻለ ክፍያውን ማቆሙን ሪፖርቶች ያሳያሉ።
ስለ ግለሰቡ ማንነት ጠለቅ ያለ መረጃ ባይገኝም ኤንአርኬ እንደዘገበው ለበርካታ ጊዜያት አግብተው እንደነበርና ልጆችም እንዳፈሩ ነው።
"በቤታቸው ካገኘናቸው ፎቶ በመነሳት ከሌሎች ጋር ብዙም ግንኙነት መፍጠር እንደማይፈልጉ ተረድተናል" በማለት ኃላፊው ይናገራሉ።
ፖሊስ ከአንድ ጎረቤት አገኘሁት ባለው መረጃ ከሰዎች ጋር ማውራት እንደማይወዱ ነው።
የግለሰቡ አሟሟት ጉዳይ ፈጥኖ አለመታወቅ አገሪቷ በቴክኖሎጂ የደረሰችበትን የላቀ ደረጃና ማህበረሰቡ እንዴት እየተቀየረ እንዳለ ማሳያ ነው ተብሏል።












