ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፈረንሳይ ውስጥ ወጣቶች መውጫ አጥቶ የነበረ አንድ ቤተሰብ ከእሳት አተረፉ
ናንት በምትባለው የፈረንሳይ ከተማ ውስጥ በአንድ የመኖሪያ ህንጻ ላይ በተከሰተ የእሳት ቃጠሎ መውጫ አጥቶ የነበረን አንድ ቤተሰብ ህይወት ያተረፉ ወጣቶች አድናቆት እየጎረፈላቸው ነው።
ወጣቶቹ ወደ ህንጻው ሦስተኛ ፎቅ ተንጠላጥለው በመውጣት ሰዎቹን ከእሳቱ እንዴት እንዳተረፉ የሚያሳየው ቪዲዮ በስፋት የታየ ሲሆን መልካም ድርጊታቸው ምስጋናን አስገኝቶላቸዋል።
በአደጋው ወቅት በህንጻው ውስጥ የነበረችን አንድ የስድስት ወር ህጻን ከእሳቱ ለማዳን ምድር ላይ በርካታ ፍራሾች ተዘርግተው ከሦስተኛ ፎቅ ላይ እንድትወረወር ተደርጋ ነበር።
ከዚህም በኋላ ህጻኗ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሆስፒታል መወሰዷ የተነገረ ሲሆን አሁን ግን እያገገመች ነው ተብሏል።
ቤተሰቡን ከእሳቱ አደጋ በማዳኑ ጥረት ውስጥ ከተሳተፉት ወጣቶች መካካል አንዱ የሆነው ታህሚድ የተባለው ወጣት ለአንድ የዜና ድርጅት እንደተናገረው ህንጻው በጭስ እየታፈነ ስለነበር ህጻኗን ከህንጻው ላይ ወደታች መወርወር "የመጨረሻው አማራጭ ነበር" ብሏል።
ከሦስተኛ ፎቅ ላይ የተነሳው እሳት ወደ ሌሎቹም የህንጻው ክፍሎች የተዛመተ ቢሆንም የእሳት አደጋ ሠራተኞች በርካታ ሰዎችን ከአደጋው አድነዋል።
የአካባቢው የወጣቶች ማኅበር መሪ ኬንዛ ዜካር፤ አደጋው ተከስቶ የእሳት አደጋ ሠራተኞች እስኪመጡ ድረስ መውጫ ያጡትን ሰዎች ለማዳን የተደረገውን ጥረት ማኅበራቸው እንዳስተባበረው ለቢቢሲ ተናግራለች።
ጨምራም በእሳቱ መውጫ አጥተው የነበሩትን ቤተሰቦች ለማዳን ወደ ህንጻው ተንጠላጥለው ከወጡት ወጣቶች መካከልም ባለቤቷ አንዱ እንደነበር ገልጻለች።
የሰዎችን ህይወት ለማዳን ጥረት ያደረጉት ሦስት ወጣቶች የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች ስለሆነ ለፈጸሙት መልካም ተግባር የመኖሪያ ሰነድና ቤት እንዲሰጣቸው የወጣቶቹ ማኅበር እየጠየቀ ነው።
ለዚህም ወጣቶቹ የጀግና ክብርና ዕውቅና እንዲያገኙ የሚጠይቅ ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት የሚቀርብ በኢንተርኔት ላይ የሚደረግ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ተጀምሯል።
ይህ ክስተት ከሁለት ዓመት በፊት ፓሪስ ውስጥ ከአንድ ህንጻ በረንዳ ላይ ተንጠልጥሎ ሊወድቅ የነበረን ህጻን በህንጻው ላይ በመንጠላጠል ያተረፈውን ከፍተኛ አድንቆትን ያገኘውን ማሊያዊ ስደተኛን አስታውሷል።
በወቅቱም ይህ ማሙዱ ጋሳማ የተባለው ስደተኛ ለፈጸመው ህጻኑን የማዳን ተግባር የአገሪቱን ፕሬዝደንት የጀግና ሜዳሊያ ተሸልሟል።