ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ኮቪድ-19 ከቻይና ቤተ ሙከራ አለመውጣቱን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ምርምራ ያስፈልጋል ተባለ
የኮሮናቫይረስ በቻይና ከሚገኝ ቤተ ሙከራ ውስጥ ሾልኮ ወጥቷል በሚለው መላምት ትክክለኛነት ዙሪያ መደምደሚያ ለማበጀት ተጨማሪ ምርመራ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ የዓለም የጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገለፁ።
ኃላፊው ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ የመውጣቱን ጉዳይ ለበሽታው መስፋፋት የመጨረሻ ምክንያት ቢሆን እንኳን፣ ይንን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የአሜሪካ መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ቻይና ለዓለም የጤና ድርጅት በቂ መረጃ አላቀረበችም ሲሉ ወቅሰዋታል። ቤይጂንግ በበኩሏ በተደጋጋሚ የቫይረሱን ከቤተ ሙከራዋ የውጣቱን ክስ ስታስተባብል ቆይታለች።
በዓለም የጤና ድርጅት እና በቻይና ባለሞያዎች ተዘጋችቶ ይፋ የሆነው ጥናት የቫይረሱ ከቤተ ሙከራ የማምጥ ጉዳይ እውነት የመሆን እድሉ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ያስረዳል። በተጨማሪም ቫይረሱ ከሌሊት ወፍ ወደ ሰው ልጅ በሌላ ሦስተኛ እንስሳ ተሸካሚነት ተላልፎ ይሆናል የሚለው ግን እውነት ሊሆን ይችላል ብሏል።
ቻይና በዚህ በአዲሱ የዓለም የጤና ድርጅት መግለጫ ላይ ገና ምላሽ አልሰጠችም።
ዶ/ር ቴድሮስ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ የሾለከ ይሆናል የሚለው መላምት ተጨማሪ ምርመራዎች ሊደረጉበት እንደሚገባ በመገለጫቸው ላይ አስረድተዋል። "እንደ የዓለም የጤና ድርጅት ሁሉም መላምቶች አጀንዳ ሆነው ይቆያሉ" ሲሉም አክለዋል።
የኮሮናቫይረስ በቻይና፣ ሁቤ ክፍለ አገር ዉሃን ከተማ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ መጀመሪያ መከሰቱ ይታወሳል። ዓለም አቀፉ የባለሞያዎች ቡድንም በያዝነው ዓመት ጥር ላይ የቫይረሱን መነሻ ለማወቅ ወደ ቻይና አቅንቶ ነበር።
የቡድኑ ምርምራም የቻይና ባለስልጣት ባቀረቡት መረጃ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነበር። ዶ/ር ቴድሮስ ቡድኑ በራሱ ጥሬ መረጃዎችን የመሰብሰብ እክሎች ገጥመውት ነበር ሲሉ ተናግረዋል። ጨምረውም የቻይና መንግሥት ለወደፊቱ ወቅታዊ እና የተሟላ መረጃን እንዲያቀርብ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በሌሊት ወፍ ላይ የሚገኘውን የኮሮናቫይረስ በተመለከተ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማከማቸትና በማጥናት በኩል የዓለማችን ቀዳሚ ተቋም የሆነውንና ቫይረሱ አፈትልኮ ወጥቶበት ይሆናል ተብሎ የተጠረጠረውን ዉሃን የቫይረስ ምርምር ተቋምን ጨምሮ ቡድኑ የተጠረጠሩ ቦታዎችን መርምሯል።
ይህን የዓለም የጤና ድርጅትን ሪፖርት ተከትሎ አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ አውስትራሊያ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ 13 አገራት ስጋታቸውን ገልጸው ቻይና ለመርማሪ ቡድኑ ሙሉ ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቀዋል።
ባወጡት መግለጫም የመርማሪ ቡድኑ ወደ ዉሃን በተጓዘበት ጊዜ "በጣም እንዲዘገይ መደረጉንና ዋነኛ መረጃዎችን እንዲሁም ናሙናዎችን በተሟላ ሁኔታ ማግኘት አልቻለም" ብለዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ያመለጠ ሳይሆን አይቀርም የሚለውን መላምት ከሚደግፉት ሰዎች መካከል ናቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት መርማሪ ቡድን መሪ የሆኑት ፒተር ቤን ኤምባሬክ ቡድናቸው ከቻይና ውጪ ሳይቀር ፖለቲካዊ ግፊት ውስጥ እንደነበረ፤ ነገር ግን ከቡድኑ የመጨረሻ ሪፖርት ውስጥ አንዳች ነገር እንዲሰርዙ ምንም አይነት ጫና እንዳልገጠማቸው ተናግረዋል።
ጨምረውም በምርመራቸው ወቅት ዉሃን ውስጥ የሚገኝ የትኛውም ቤተሙከራ ለወረርሽኙ መከሰት አስተዋጽኦ እንዳለው የሚያመለክት ምንም አይነት ማስረጃ እንዳላገኙ መስክረዋል።