ፌስቡክ የዶናልድ ትራምፕን ድምጽ ከገጹ ላይ አገደ

ፌስቡክ የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዝዳንት የዶናልድ ትራምፕ ተንቀሳቃሽ ምስልን ከልጃቸው ሚስት ላራ ትራምፕ ገጽ ላይ አወረደ።

ግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ ተቋም የትራምፕን ምስል ከገጹ ላይ ያነሳው በታኅሣሥ ወር ላይ ነውጠኛ ደጋፊዎቻቸው ዋሺንግተን የሚገኘውን ካፒቶል ሒል ህንጻ ካጠቁ በኋላ ነበር።

ላራ ትራምፕ ፎክስ ኒውስ ላይ አልፎ አልፎ የምትቀርብ ሲሆን አማቿ የሆኑትን ትራምፕን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ቃለመጠይቅ አድርጋላቸው ነበር።

በኋላ ላይም ፌስቡክ በኢሜል አድራሻዋ የጻፈላትንና ልትታገድ እንደምትችል የሚገልጸውን መልዕክት ፎቶ አንስታ አጋርታለች።

"ዶናልድ ትራምፕን ከፌስቡክ እና ከኢንስታግራም ለማገድ ባስቀመጥነው መመሪያ መሰረት የዶናልድ ትራምፕን ድምጽ የያዘ መልዕክት ወዲያውኑ ይነሳል፤ በተጨማሪም በአካውንቱ ላይ ተጨማሪ እቀባ ይደረጋል" ይላል በካትሊን የተጻፈው ይህ ኢሜል።

የዶናልድ ትራምፕን ልጅ ኤሪክ ትራምፕን ያገባችው፤ ላራ ትራምፕ በኢንተርኔት ላይ በሚቀርበው የራሷ ፕሮግራም ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ያደረገችውን ቆይታ በቀጥታ ከመጫን ይልቅ ማስፈንጠሪያውን በገጿ ላይ አስቀምጣ ነበር።

ፌስቡክ ትራምፕን ከገጹ ላይ ያገዳቸው በፈረንጆቹ ታኅሣሥ 7/2020 ነውጠኛ ደጋፊዎቻቸው የአሜሪካ ምክር ቤት መቀመጫ የሆነውን የካፒቶል ሒል ህንጻን ከወረሩና ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው።

በወቅቱ ማርክ ዙከርበርግ ውሳኔውን በተመለከተ ሲናገር "ፕሬዝዳንቱ በዚህ ወቅት የእኛን አገልግሎት እንዲጠቀሙ መፍቀድ ያለው አደጋ ከፍተኛ መሆኑን እናውቃለን" ብሎ ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ከትዊተር እና ከዩቲዩብም መታገዳቸው ይታወሳል።