ፕሬዝዳንት ትራምፕ ትዊተርን እንዳይጠቀሙ አስከመጨረሻው ታገዱ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ተጨማሪ የኃይል ድርጊቶችን ሊቀሰቅሱ ይችላሉ" በሚል ስጋት በዘላቂነት ትዊተር ገጽ ላይ ድርሽ እንዳይሉ ኩባንያው እግድ ጣለባቸው።

ትዊተር ጉዳዩን አስመልክቶ እንዳለው በትራምፕ ላይ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ፕሬዝዳንቱ በአካውንታቸው ላይ "በቅርቡ ያሰፈሯቸውን መልዕክቶች በደንብ ከመረመረ" በኋላ መሆኑን ገልጿል።

አንዳንድ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎችና ታዋቂ ሰዎች ትራምፕ ከትዊተር አስከወዲያኛ እንዲታገዱ ለዓመታት ሲወተውቱ ቆይተዋል።

የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ ሐሙስ ዕለት በትዊተር ገጻቸው ላይ የማኅበራዊ ሚዲያ ተቋማት ዶናልድ ትራምፕን ከመድረኮቻቸው በማስወገድ "በአደገኛ ባሕሪያቸው" እንዲገፉበት ከማድረግ እንዲቆጠቡ ጠይቀው ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ረቡዕ ዋሽንግተን ውስጥ የሚገኘውን ካፒቶል ሒልን የወረሩትን ደጋፊዎቻቸውን "አርበኞች" በማለት ካሞገሱ በኋላ ለ12 ሰዓታት ትዊተርን እንዳይጠቀሙ ታግደው ነበር።

የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት የጆ ባይደንን የምርጫ ውጤት ለማረጋገጥ ተሰብስበው ባሉበት በመቶዎች የሚቆጠሩት የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች ወደ ምክር ቤቱ ግዙፍ ሕንጻ ጥሰው በመግባት በተፈጠረ ግርግር አንድ ፖሊስን ጨምሮ የአምስት ሰዎች ህይወት አልፏል።

ይህንንም ተከትሎ ትዊተር ፕሬዝዳንት ትራምፕ በድጋሚ የማኅበራዊ መድረኩን ደንቦች የሚጥሱ ከሆነ "እስከወዲያኛው" እንዳይጠቀሙ እገዳ እብደሚጥልባቸው አስጠንቅቆ ነበር።

ነገር ግን ከሰዓታት በኋላ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አካውንት መልሶ ቢከፈትም በድጋሚ አርብ ዕለት በሰሌዳቸው ላይ በለጠፏቸው ሁለት መልዕክቶች ሳቢያ አስከመጨረሻው ታገደዋል።

ትዊተር እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ያስገደዱት የመጨረሻዎቹ መልዕክቶች ፕሬዝዳንቱ የድርጅቱን ፖሊሲ በመቃረናቸው መሆኑን አመልክቷል።

ፕሬዝዳንት ትራም በአንደኛው መልዕክታቸው ላይ "እኔን የመረጡ 75 ሚሊዮን አሜሪካውያን ወደፊት ታላቅ ድምጽ ይኖራቸዋል። በየትኛውም መንገድም ሆነ አይነት ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ሊስተናገዱና አክብሮትን ሊነፈጉ አይገባም!!" በማለት አስፍረው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ትዊተር እንዳለው "ይህ መልዕክታቸው ፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ሽግግርን በአግባቡ ለማካሄድ ፍላጎት እንደሌላቸው በሚያሳይ ሁኔታ ተተርጉሟል" በማለት ለውሳኔው ምክንያት አቅርቧል።

ፕሬዝዳንቱ በሁለተኛው መልዕክታቸው ደግሞ "ለጠየቃችሁኝ ሁሉ፤ [በጆ ባይደን] ሲመተ በዓል ላይ አልገኝም" ሲሉ ከሁለት ሳምንት ባለሰ ጊዜ ውስጥ በሚከናወነው የሥልጣን ርክክብ ላይ እንደማይሳተፉ ገልጸዋል።

ትዊተር ይህንን መልዕክታቸውን በተመለከተም "ይህ በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ዘንድ ምርጫው ሕጋዊ እንዳልሆነ እንደተጨማሪ ማረጋገጫ ተደርጎ ተወስዷል" ብሏል።

በዚህም መሠረት ትዊተር እነዚህ የፕሬዝዳንቱ የትዊተር መልዕክቶች የድርጅቱን "የኃይል ድርጊትን የማበረታታት ፖሊሲን የሚጻረሩ ናቸው" በማለት ትራምፕን አስከመጨረሻው ከሚወዱት የትዊተር መድረክ ላይ አሰናብቷቸዋል።