ኮቪድ-19፡ ጭምብል ባለማድረጉ የኦቲዝም ተጠቂ ህጻንን ከአውሮፕላን ያስወረደው አየር መንገድ ወላጆቹን አስቆጣ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካ የኦቲዝም ተጠቂ የሆነ የአራት ዓመት ህጻን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ባለማድረጉ ከአውሮፕላን እንዲወርድ መደረጉ ቤተሰቦቹን አስቆጣ።
የህጻኑ እናት እንደምትለው አየር መንገዱ አካል ጉዳቱን ለመረዳት ባለመፈለጉና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርግ ካስገደደው በኋላ ህጻኑ ከአውሮፕላኑ ሊወርድ ችሏል።
ስፕሪት አየር መንገድ ጉዳዩን በተመለከተ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገረው፤ ከሁለት ዓመት በታች ከሆኑ ህጻናት በስተቀር ሁሉም ተሳፋሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ አለባቸው።
የአሜሪካ መመሪያ ግን በሕክምና የተከለከሉ መንገደኞች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ አይጠበቅባቸውም ይላል።
የህጻኑ እናት ልጇ ከዚህ በፊት አውሮፕላን ይወድ እንደነበር ገልጻ ከአውሮፕላኑ እንዲወርድ ከተደረገ በኋላ ግን መረበሹን ተናግራለች።
ካሌ ኪምቦል ሰኞ ዕለት ከወንድ ልጇ ካርተር እና ባለቤቷ ጋር ከላስቬጋስ እየተጓዙ ነበር።
የልጇንም የጤንነት ሁኔታ የሚያስረዳ የሕክምና ማስረጃ ይዛ እንደነበረ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ተናግራለች።
"የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሲያደርግ ትንፋሹን ስለሚይዝና መጨነቅ ስለሚጀምር፤ ራሱን እንዳይጎዳ በሚል እንዳያደርግ ተከልክሏል። " ስትል ልጇ የኦቲዝም ተጠቂ እንደሆነና መናገር እንደማይችል አስረድታለች።
ይሁን እንጅ ባለቤቷ የሕክምና ማስረጃውን በላስ ቬጋስ ለሚገኙ የአየር መንገዱ የበረራ ቡድን አባል በሚያሳይበት ጊዜ " አይሆንም! ኦቲዝም የአካል ጉዳት አይደለም። በመሆኑም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛውን ማድረግ አለበት አሊያም ከአውሮፕላኑ መውረድ አለበት" መባሉን የካርተር እናት ተናግራለች።
በዚህም የተነሳ እነዚህ ቤተሰቦች አየር መንገድ ቀይረው በአሜሪካ አየር መንገድ ወደ መኖሪያቸው አርካስናስ መሄድ ችለዋል።
ይህ አየር መንገድም የልጇን የሕክምና ማስረጃ መቀበሉን ኪምቦል አክላለች።
ስፕሪት አየር መንገድ በበኩሉ "ያለን ነባር ሕግ ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አለማድረግን አይፈቅድም። ቡድናችንም ይህንኑ ለቤተሰቦቹ አስረድቷል። ነገር ግን በዚህ ሂደት አየር መንገዱ የማንም የጤና ሁኔታ ላይ ጥያቄ አላነሳም" ብሏል።
አየር መንገዱ ለሲቢኤስ ኒውስ እንዳለው ሕጉ ከሁለት ዓመት በታች ካሉ ህጻናት በስተቀር ማንኛውም ደንበኛ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ ያዛል።
ከመጋቢት 22 በኋላ ግን የአካል ጉዳት ያለባቸው መንገደኞች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዳያደርጉ መጠየቅ እንደሚችሉ ድርጅቱ ጠቁሟል።
የአሜሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማንኛውም የአየር መንገደኞች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንዳለባቸው የካቲት ወር ላይ መመሪያ አውጥቷል። ይሁን እንጂ የአካል ጉዳት ያለባቸውና ማድረግ የማይችሉት በዚህ አይካተቱም ብሏል።
አሜሪካ አየር መንገድና አላስካ አየር መንገድን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ፖሊሲያቸው ነጻ ናቸው።
ኪምቦል "ልጄ አውሮፕላን ይወዳል፣ በራሱ ወንበር ላይ ተቀምጦ፣ በፀጥታ በመስኮት ውጩን እየተመለከተ ሳለ ነው ይህች ሴት መትታ 'ውረድ!' ያለችው" ትላለች በሀዘኔታ።
ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት መገለል ገጥሟት እንደማያውቅም ተናግራለች።
መስከረም ወር ላይ አንድ የሦስት ዓመት የኦቲዝም ተጠቂ ልጅ እናት፤ ስፕሪት አየር መንገድ ልጇ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ባለማድረጉ በአውሮፕላኑ እንዳይጓዝ እንዳገደው ተናግራለች።
አየር መንገዱ ግን ልጁ ከአውሮፕላኑ እንዲወርድ የተደረገው ተሳፋሪዎችን መሳደብ በመጀመሩ ነው ብሏል።













