’ኮሮናቫይረስ፡ ካልተከተቡ አይቀጠሩም’ የሚል ህግ ለአዳዲስ ሠራተኞች ተግባራዊ ሊሆን ይችላል

ኩባንያዎች አዳዲስ ሠራተኞቻቸው፣ ከመቀጠራቸው በፊት እንዲከተቡ ቢጠይቁ ህጋዊ ሊሆን ይችላል ሲሉ የእንግሊዝ የፍትህ ሚንስትር አስታወቁ።

እንደሮበርት ባክላንድ ከሆነ ነባር ሠራተኞች ባላቸው ውል መሠረት ክትባቶችን እንዲወስዱ የመጠየቅ ነገር ላይኖር ይችላል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ሰዎች በሥራቸው እንዲቀጥሉ ክትባት እንዲወስዱ ማዘዙ "አድሎአዊ" ነው ብሏል።

ነገር ግን አንዳንድ ድርጅቶች ክትባቱን ለመውሰድ ፈቃደኛ ያልሆኑ አዳዲስ ሠራተኞችን እንደማይቀጥሩ ይናገራሉ፡፡

ባክላንድ ረቡዕ ዕለት ከአይቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አዳዲስ በሥራ ውል ላይ በጽሑፍ እስከቀረበ ድረስ ሠራተኞችን እንዲከተቡ ማስገደድ ይቻል ይሆናል ብለዋል፡፡

ሆኖም አሠሪዎች ምናልባት ነባር ሠራተኞች እንዲህ ዓይነቱን ትዕዛዝ እምቢ ካሉ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ሊያስፈልጋቸው ይችላል ተብሏል።

አክለውም "ያለ ክትባት ሥራ የለም" የሚሉት መስፈርት ሕጋዊነት "በቅጥርና በልዩ ውል ላይ የተንጠለጠለ ነው" ብለዋል፡፡

"በአጠቃላይ አካሄዱን ሕጋዊ ያደረጉት አሁን ያሉት የሥራ ኮንትራቶች ቢኖሩ እደነቃለሁ፡፡ እውነቱን ለመናገር ጉዳዩ መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል" ብለዋል፡፡

መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የፒምሊኮ ፕለምበርስ ከህክምና ጋር በተያያዘ ካልሆነ በስተቀር ክትባቱን አልፈልግም የሚሉ አዳዲስ ሠራተኞችን አልቀጥርም ካሉት ኩባንያዎች አንዱ ነው፡፡

ከቅጥር ጋር በተያያዘ የሚሠሩ የህግ ባለሙያዎች በመጀመሪያ እርምጃው ላይ ጥያቄ ቢያነሱም መስራቹ ቻርሊ ሙሊንስ ህጋዊ እንደሆነ ምክር እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

"እኛ በግልጽ ከጠበቆች ጋር የተነጋገርን ሲሆን ክትባቱ ሙሉ በሙሉ ከወጣ በኋላ ከእኛ ጋር ለሚጀምሩ ማናቸውም አዳዲስ ሠራተኞች የክትባቱ ጉዳይ በውሉ ውስጥ በመካተቱ ባለሙያዎቹ በጣም ደስተኞች ናቸው" ብለዋል ለቢቢሲ፡፡

"አዲሶቹን ኮንትራቶች ከሁለት እስከ ሶስት ወራቶች ውስጥ እንጠቀማቸዋለን፡፡ ሰዎች ከእኛ ጋር ሥራ ለመሥራት ሲመጡ ያንን በመፈረም ደስተኛ ካልሆኑ የእነሱ ምርጫ ነው። በእርግጠኝነትም ሥራው ከፒምሊኮ ፕላምበርስ አይሰጣቸውም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የቤት እንክብካቤ ላይ የተሠማራው ባርቸስተር ሄልዝኬርም ሁሉም አዲስ ቅጥር ሠራተኞችየመከተብ ግዴታ አለባቸው ብሏል፡፡

"ከሠራተኞቻችን ጋር በተያያዘ ፍላጎት ያላቸውን ክትባቱን እንዲያገኙ ለማበረታታት የተቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው። በተጨማሪም ሁሉም አዲስ ሠራተኞች ክትባቱን መውሰዳቸውን ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ማረጋገጥ አለብን" ያለው ድርጅቱ ደንበኞቹን እና ሠራተኞቹን ጤንነት መጠበቅን ደግሞ በምክንያትነት አስቀምጧል።

'የህግ ክፍተት'

ሌዊስ ሲልኪን በሚባለው የሕግ ኩባንያ የሕግ ዳይሬክተር የሆኑት ዴቪድ ሳሙኤል እንዳሉት ድርጅቶች በአዳዲስ ቅጥር ሠራተኞቻቸው ኮንትራቶች ውስጥ "ያለ ክትባት ሥራ የለም" የሚል አንቀጽን ከማስገባት የሚያግዳቸው ሕጋዊ ማዕቀፍ የለም፡፡

አሠሪዎች እያንዳንዱን የሥራ ሚና መተንተን እና እንዲህ ዓይነቱን ሐረግ ከማስተዋወቅ በፊት የጤና እና የደህንነትን አደጋዎችን መገምገም አለባቸው ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

ይህ ባለማድረጉና አንድ ሠራተኛ ያልተከተበት ምክንያት ቢኖረው ውሉ ኢ-ፍትሃዊ ወይም አድሎአዊ ነው ብሎ ለመከራከር ያስችለዋል፡፡

ሌሎች ስጋቶችም አሉ። ለምሳሌ ፣ "ካልተከተቡ ሥራ የለም" የሚለው ፖሊሲ ክትባቱን ለመውሰድ የመጨረሻ መስመር ላይ ባሉ ወጣቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ የሚል ስጋት አለ፡፡

"ይህን ለማጽደቅ ከባድ ይሆናል። በተለይም በዚያ ሂደት ውስጥ ካልገቡ እና ካልሰነዱት በሕጋዊ ጥያቄ የመፈታተናቸው ዕድላቸው ሰፊ ነው" ሲሉ ሳሙኤል ለቢቢሲ ገልጸዋል፡፡

የአንዳንድ ሠራተኞች የሥራ ሁኔታ በቢሮ ወይም በፋብሪካ እንዲሠሩ የሚያስገድድ ከሆነ ድርጅታቸው እንደዚህ ዓይነት አንቀፅ ሊቀመጥ ይችላል ወይ የሚል ጥያቄ እንደደረሳቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

"ክትባት መውሰድ ግዴታ አይደለም፤ እናም አንድ ሰው እንዲወስድ ማስገደድ አድልአዊ ነው" ብለዋል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ፡