ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሞቃዲሾ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ጥቃት መፈጸሙ ተነገረ
ታጣቂዎች ሞቃዲሾ ውስጥ ለሚገኘው ቤተ መንግሥት ቅርብ በሆነ አንድ ሆቴል ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን የሶማሊያ መንግሥት ተገለፀ።
የአገሪቱ የደኅንነት ሚኒስትር ዛሬ ማለዳ በሰጡት አጭር መግለጫ ላይ ጥቃቱ ከሽፏል ብለው ነበር።
ዛሬ ማለዳ በሞቃድሾ በሚገኘው አደን አዴ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በረራ መቋረጡን ቢቢሲ አረጋገጠ።
በአውረሮፕላን ማረፊያው አቅራቢያ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር የተዘገበ ሲሆን፣ ዛሬ ጠዋት ወደ ዋና ከተማዋ በረራ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉዞ መሰረዙን የአውሮፕላን ማረፊያው የውስጥ ምንጮች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ትናንት ምሽት ጥቃቱ በተፈፀመበት ስፍራ አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች እንደተናገሩት ትናንት ምሽት ከባድ የመሳሪያ ተኩስ ሰምተው ነበር።
ይህ ጥቃት የተፈፀመው የሶማሊያ ተቃዋሚዎች የፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፎርማጆ የሥልጣን ዘመን ማብቃትን ምከንያት በማድረግ ተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ማቀዳቸውን ከተሰማ ከሰዓታት በኋላ ነው።
የፕሬዝዳንት ፎርማጆ የሥልጣን ዘመን ያበቃው ባለፈው ሳምንት ሲሆን ይህም አገሪቷን የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ከትቷል።
ፕሬዝዳንቱ ከአምስት የክልል ፕሬዝዳንቶች ጋር አገሪቱ ከገባችበት አጣብቂኝ እንዴት መውጣት እንደምትችል ምክክር ያደርጋሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
የመንግሥት ወታደሮች እና ለዕጩዎች ታማኝ የሆኑ ታጣቂዎች ትናንት ምሽት ለቤተመንግሥቱ ቅርብ በሆነው ማይዳ ሆቴል አካባቢ ነበር የተኩስ ልውውጥ ያደረጉት።
በዚህ ሆቴል ውስጥ ሁለት የአገሪቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች፣ ሼክ ሻሪፍ እና ሀሰን ሼክ ይገኙ ነበር።
የፌደራል መንግሥቱ እና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጥቃቱን በሚመለከት እርስ በእርስ እየተወነጃጀሉ ነው።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ ለጥቃቱ የፌደራል መንግሥቱን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፣ ዜጎች በሰላም ተቃውሟቸውን ለመግለጽ በሚዘጋጁበት ወቅት የሥልጣን ዘመናቸው ያበቃው ፕሬዝዳንት "ከዜጎች ጋር ደም ለመቃባት ማሰባቸው" ያሳዝናል ብለዋል።
ለዚህ ውንጀላ ምላሽ የሰጡት የአገሪቱ ደኅንነት ሚኒስትር ጥቃቱ የተፈፀመው በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተወዳዳሪ እጩዎች ነው ብለዋል።
አክለውም የመንግሥት ወታደሮች ጥቃቱ ምላሽ መስጠታቸውንና መከላከላቸውን ገልፀዋል።
በአሁን ሰዓት ሞቃዲሾ መንገዶች ዝግ ሲሆኑ፣ በአውራ ጎዳናዎችም ልዩ ስልጠና የወሰዱ ወታደሮች ተሰማርተው ጥበቃው ተጠናክሯል።
ተቃዋሚዎች ዛሬ በከተማዋ ጠርተውት የነበረውን የተቃውሞ ሰልፍ የሶማሊያ ብሔራዊ ወታደራዊ ኃይል አባላት ተኩስ ስለከፈቱባቸው እንዲቋረጥ አድርገዋል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ቀጣይ እርምጃቸውን ለማስታወቅ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የሥልጣን ዘመናቸው ያበቃውን ፕሬዝዳንት ፎርማጆን ከሥልጣን እንዲወርዱ ጠይቀዋል።
በትናንትናው ምሽት ጥቃት ምን ያህል ሰው ጉዳት እንደደሰበት የታወቀ ነገር የለም። በሶማሊያ የፖለቲካ ውጥረቱ እና ቀውሱ እየከፋ ይሄዳል የሚል ስጋት በበርካቶች ዘንድ እየተስተዋለ ነው።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አራት ዓመት የሥልጠና ዘመን ያበቃው ባለፈው ሳምነት ሲሆን ተቃዋሚዎች ከአሁን በኋላ ለፕሬዝዳንቱ እውቅና እንደማይሰጡ ተናግረዋል።
መንግሥት በበኩሉ አዲስ አስተዳዳር እስኪመረጥ ድረስ ፕሬዝዳንቱ ስልጣናቸው ላይ ይቆያሉ ብሏል።
አዲሱ አስተዳደር መቼ ይመረጣል የሚለው ግን የታወቀ ነገር የለም።