"አቶ በቀለ በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ጦር ኃይሎች መወሰዳቸው ከህግ አግባብ ውጭ ነው" ጠበቃቸው

የተቃዋሚ ፓርቲ ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀ መንበርና በረሃብ አድማ ላይ የሚገኙት አቶ በቀለ ገርባ በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ መንግሥታዊው የጤና ማዕከል ጦር ሃይሎች ሆስፒታል መወሰዳቸውን ቢቢሲ ከጠበቃቸውና ከሃኪማቸው መረዳት ችሏል።

ከአቶ በቀለ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ መሃመድ ጅማ፤ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመተላለፍ አቶ በቀለ ወደ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል በኃይል መወሰዳቸው "ከህግ አግባብ ውጭ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብር እና በሕገ-መንግስት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ችሎት ሰኞ እለት የካቲት 8፣ 2013 ዓ.ም እነ አቶ በቀለ ገርባን በግል የጤና ተቋም በሆነውና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ላንድ ማርክ ሆስፒታል እንዲታከሙ ውሳኔ አስተላልፏል።

ይህንን የፍርድ ቤት ውሳኔ በዚያኑ ዕለት፣ ሰኞ ጠበቆቻቸው ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዳስገቡና ደብዳቤውንም እንደተቀበሏቸው አቶ መሃመድ አስረድተዋል።

ከጥር 19፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ያለ ውሃ ምንም የማይቀምሱትና የረሃብ አድማ ላይ ናቸው የተባሉት አቶ በቀለ የጤና ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታም በማሽቆልቆሉ ሃኪሞቻቸው ተኝተው እንዲታከሙ ውሳኔ ላይ መደረሱን ዶክተር ኢሊሊ ይናገራሉ።

በትናንትናውም ዕለት የካቲት 9፣ 2013 ዓ.ም ዶክተር ኢሊሊ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ በቀለ ገርባን ለመውሰድ ጥዋት 4፡00 አካባቢ እንደደረሱ ገልፀዋል።

ማረሚያ ቤቱ የሚያከናውናቸውን ስራዎችን ጨርሶ ወደ ምሳ ሰዓት አካባቢ ላንድ ማርክ ሆስፒታል ለመውሰድ ጉዞ ጀመሩ።

ሃኪማቸው ዶክተር ኢሊሊ፣ ጠበቆቻቸው፣ ቤተሰባቸው፣ አቶ በቀለና ማረሚያ ቤቱም የሚያውቁት ወደ ላንድ ማርክ ሆስፒታል እንደሚሄዱ ነው።

በአምቡላንስ ተጭነው ወደ ላንድ ማርክ እየሄዱ በነበረበት ወቅት አፍሪካ ህብረት አካባቢ አንድ ነጭ ፒክ አፕ መኪና መንገድ እንደዘጋባቸውና አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር በቦታው የነበሩት ዶክተር ኢሊሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ከላይ በመጣ ትዕዛዝ መሰረት ወደ ላንድ ማርክ ሆስፒታል ሳይሆን ወደ ጦር ሃይሎች ሆስፒታል መወሰድ እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል።

ይኼንን ለአቶ በቀለ በሚነግሯቸው ወቅት ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት "መልሱኝ" በማለት ጥያቄ ማቅረባቸውንም ዶክተር ኢሊሊ ያስረዳሉ።

ከአቶ በቀለ በተጨማሪ ዶክተር ኢሊሊም እንዲሁ ወደ ላንድ ማርክ መውሰድ የማይቻል ከሆነ ወደ ቃሊቲ እንዲመልሱዋቸው መጠየቃቸውን ይናገራሉ። በምላሹ ግን "በኃይል" ወደ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል እንደወሰዷቸው ይናገራሉ።

"ወደ ላንድ ማርክ መውሰድ ካልቻላችሁ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውሰዱን እያልን እየጠየቅን እያለ እምቢ ብለው፣ ያለኛ ፈቃድ በግድ ወደ ጦር ሃይሎች ሆስፒታል ይዘውን ሄዱ" ይላሉ።

ጦር ሐይሎች ሆስፒታል ከደረሱም በኋላ አቶ በቀለ አልታከምም እንዳሉና የማረሚያ ቤት ሰዎችም መመለስ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለአራት ሰዓታት ያህል በሆስፒታሉ እንደቆዩ ዶክተሯ ይናገራሉ።

"አቶ በቀለ 'እኔ በፍፁም ፍርድ ቤት የፈቀደልኝ ቦታ ነው የምታከመው። ከፍርድ ቤት በላይ ሆናችሁ ያንንም ከወሰናችሁ መብታችሁ ነው ቢያንስ ወደማርፍበት ክፍል ውሰዱኝ ብለው ለመኑ'" በማለት ዶክተሯ የሆነውን ያስረዳሉ።

በወቅቱም የማረሚያ ቤቶቹ ሰዎች ለማግባባት እንደሞከሩና እንዲሁም ከላይ ተፃፈ የተባለው የትዕዛዝ ደብዳቤ በጠቅላይ አቃቤ ህግ ጌዴዎን ጤሞቴዎስ የተፈረመ ደብዳቤ እንዳሳዩዋቸውም ይናገራሉ።

ደብዳቤው የተፃፈው ለማረሚያ ቤቱ ሲሆን የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲቀየር ጠቅላይ አቃቤ ህግ ይግባኝ መጠየቁንና ይህ እስኪሆን በመንግሥት ተቋማት ነው መታከም የሚችሉት የሚል ይዞታ ያለው ደብዳቤ እንዳዩ ይናገራሉ።

የአቶ በቀለ ጠበቃ አቶ መሃመድም በዛሬው ዕለት የማረሚያ ቤቶቹን ኃላፊዎች ባናገሯቸው ወቅት የጠቅላይ አቃቤ ህግ የዶክተር ጌዴዎን ደብዳቤ በቴሌግራም ደብዳቤ እንደደረሳቸውና "ትዕዛዙን ለማስቀየር ፍርድ ቤት ማመልከቻ አስገብተናልና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እስከምናወጣ ድረስ የግል ሆስፒታል እንዳይሄዱና ወደ ጦር ሃይሎች ሆስፒታል እንዲወሰዱ የሚል ነው"።

ምንም እንኳን ማረሚያ ቤቱ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሆንም ነገሩን የተረዱት መንገድ ላይ እንደሆነም አቶ መሃመድ ከማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ተረድተዋል።

አቶ መሃመድ እንደሚሉት ጠቅላይ አቃቤ ህግ ደብዳቤ ለማረሚያ ቤቱ ቀደም ብሎ መፃፍ ሲችል "መንገድ የተዘጋበትን ሁኔታ" አለመረዳታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ደንበኛቸው አቶ በቀለ "በሃይል መወሰዳቸው ከህግ አግባብ ውጭ መሆኑ" እንዲሁም "በፀጥታ ኃይሎች መንገድ በመዝጋት" የተሰራው አሰራር ትክክል እንዳልሆነ ይናገራሉ።

"ጠቅላይ አቃቤ ህግ የፍርድ ቤት ትእዛዝ ማገድ አይችልም እንዲሁም ሁለቱም የመንግሥት አካል ሆነው ሌላኛው አካል መንገድ በመዝጋት በኃይል ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር" ትክክል እንዳልሆነም ጠቁመዋል።

ቢቢሲ የጠቅላይ አቃቤ ህግ አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ፍርድ ቤቱም በዛሬው ዕለት የጠቅላይ አቃቤ ህግን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ በግል ሃኪም ቤት እንዲታከሙ መወሰኑን አቶ መሃመድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤቱ በግል ሃኪም ቤት እንዲታከሙ የወሰነላቸው ሲሆን የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በበኩሉ የፀጥታና ደህንንነት በተመለከተ ያለውን ሁኔታ አቅርቦ ይግባኝ የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱም የካቲት 2፣ 2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት ወደ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል እንዲወሰዱ ወስኖ ነበር።

በወቅቱ ማረሚያ ቤቱ ታሳሪዎቹ የረሃብ አድማ ላይ በመሆናቸው "ታመው ከወደቁ ዝም ብለን ማየት ስለማንችል፤ ቀደም ብለው ስለማይነግሩንና በዛ አጭር ሰዓት ውስጥ እነሱ የፈለጉት ሆስፒታል ላይ ሃይል አሰባስበን ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ስለምንቸገር፤ ድንገት ከወደቁ ግን ጦር ሃይሎች ሆስፒታል እንድናሳክም ይፈቀድልን" ብለው በማመልከታቸው ለጊዜው ፍርድ ቤቱ ይኼንን ፈቅዶላቸው እንደነበር አቶ ጅማ ያስረዳሉ።

ጠበቆቻቸው በበኩላቸው ሆስፒታሉን ከስምንት ሰዓት በፊት እንደጠየቁና ደንበኞቻቸው በመረጡት ሆስፒታል እንዲታከሙ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲያስተላልፍና ከዚህ ቀደም የነበረውን ውሳኔ እንዲያፀና ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም ውሳኔውን በመቀልበስ እነ አቶ በቀለ በላንድ ማርክ ሆስፒታል እንዲታከሙ ውሳኔ አስተላልፏል። በዚህም ውሳኔ መሰረት ነው በዶክተር ኢሊሊ አጃቢነት አቶ በቀለ ገርባ ወደ ላንድ ማርክ ሆስፒታል የተወሰዱት ።

ከዚህ ቀደምም ለሳምንታት ያህል ህክምና አሻፈረኝ ብለው የነበሩት አቶ በቀለን በማግባባትና ከማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ጋር ወደ ግል ሆስፒታል ለመውሰድ ተስማምተው ነበር።

የካቲት 5 የህክምና ቡድኑ ቃሊቲ የፌደራል ማረሚያ ቤት ከደረሱ በኋላ ግን መንግሥት ሆስፒታል ነው መወሰድ የሚችሉት ተብሎ ተነግሯቸዋል።

የጤና ሁኔታቸው እያሽቆለቆለ የሚገኙት አቶ በቀለን ወደ ግል ሆስፒታል ለመውሰድ በሚሞክሩበት ወቅት የማረሚያ ቤቱ አስተዳደሩ ማስቆሙን ተከትሎ ዶክተር ኢሊሊ ስራ ማቆማቸውን ተናግረው ነበር።

ጠበቃቸው መሃመድም እንዲሁ አርብ በ5፣ 2013 ዓ.ም ሆስፒታል ባለመግባታቸው ያንን ቅሬታ ገልፀው በያዝነው ሰኞ ፍርድ ቤት ማመልከቻ ማስገባታቸውን ይናገራሉ።

"እኛ ማከሙን አቁመናል ስለተገደድን፤ ለማከም ሆስፒታል መውሰድ አልቻልንም። በዚህ ወቅትም መቻላችንንነ አናውቅም። ተመልሰን መጀመሩ ራሱ ያስፈራናል" በማለትም ሰኞ እለት ለዋለው ችሎት ዶክተር ኢሊሊ አስረድተዋል።

በምላሹም ዶኞቹ ውሳኔው እንዲፀናና በግል ሃኪም ቤት እንዲታከሙና የህክምና ባለሙያዎቹም ተመልሰው ስራቸውን እንዲጀምሩና እንዲከታተሏቸው መጠየቃቸውን ዶክተሯ ይናገራሉ።

በትናንትናው ዕለት አቶ በቀለ ምንም ዐይነት ህክምና ሳያገኙ "ተንገላተው ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በመመለሳቸው" የጤና ሁኔታቸውን አሳሳቢ እንዳደረገው ዶክተሯ አልደበቁም።

"ትናንት የተፈጠረው ነገር ይበልጥ እንድንፈራና እንድንጠራጠር አድርጎናል። አሁን ባለው ሁኔታ እኛ መልሰን ጤናቸውን የመከታተል ሃሳቡም የለንም። ለራሳችን እየፈራን ነው" ይላሉ ዶክተር ኢሊሊ

እነ አቶ በቀለ የረሃብ አድማውን እያደረጉ ያሉት በፖለቲከኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልት እና እስር፣ እነሱን ለመጠየቅና የችሎት ሂደታቸውን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በሚሄዱ ሰዎች ላይ የሚፈጸም እስር እና ወከባ እንዲቆም ለመጠየቅ እንደሆነ ቢቢሲ ከጠበቆቻቸው ለመረዳት ችሏል።

እነ አቶ ጃዋር እና አቶ በቀለን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞች የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከት ጋር ተያይዞ እጃችሁ አለበት ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የሚታወስ ነው።

ከቀረቡባቸው ተደራራቢ አስር ክሶች መካከል ስድስቱ እንዲቋረጡ ፍርድ ቤት ጥር ወር ላይ መወሰኑ ይታወሳል።

የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ፣ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ፣ የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ የመተላለፍ ክሶች ከተመሰረቱባቸው ክሶች መካከል ሲሆኑ፤ እንዲቋረጡ የተደረጉት ክሶች የጦር መሣሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2021 የተያያዙ ሲሆኑ በወቅቱ ውሳኔ እንዲቋረጡ የተደረጉት ክሶች የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2021 የተያያዙ መሆናቸውም የሚታወስ ነው።