ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዓለም ላይ በጣም ኃይለኛ የሆኑት የመሬት መንቀጥቀጦች የትኞቹ ነበሩ? ለምን ሱናሚ ያስነሳሉ?
ባለፈው ሳምንት በሩሲያ ካምቻትካ ባሕረ ገብ መሬት አካባቢ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በ8.8 በሬክተር ስኬል የተመዘገበ ሲሆን፣ እስካሁን ከተመዘገቡት ርዕደ መሬቶች ሁሉ እጅግ ጠንካራው ነው።
ማለዳ 11፡25 ላይ የተከሰተው ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ ከባሕር ላይ የሱናሚ ማዕበልን ቀስቅሶ በሩሲያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ በጃፓን እና በፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ቤታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ እንዲሰጥ አድርጓል።
በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ አካባቢዎች የመሬት ነውጥ የሚከሰት ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ እንደ ነውጡ መጠን በሰው እና በንብረት ላይ አደጋን ያደርሳል።
በባሕር እና ውቅያኖሶች ላይ የሚከሰተው ርዕደ መሬት መጠኑ ከፍተኛ ከሆነ ውሃውን በከፍተኛ ኃይል እና ፍጥነት በመግፋት በምድር ላይ ጉዳትን ያስከትላል።
እስካሁን በዓለም ዙሪያ ደርሰው ተመዘገቡት ኃያል የመሬት መንቀጥቀጦች የትኞቹ ናቸው? ሱናሚስ ለምን ያስነሳሉ?
ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጦች
ዘመናዊ የመሬት መንቀጥቀጥ ጥናት (seismology) ከጀመረበት ከአውሮፓውያኑ 1900 አንስቶ በሩሲያ የባሕር ዳርቻ ከተከሰተው እና በርዕደ መሬት መለኪያ 8.8 ከተመዘገበው የበለጠ ጠንካራ የሆኑ አምስት የመሬት መንቀጥቀጦች ብቻ ነበሩ።
በዩናይትድ ስቴትስ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ (USGS) መረጃ መሠረት እጅግ በጣም ኃይለኛ የሆነው በቺሊ በአውሮፓውያኑ 1960 የተከሰተው እና 9.5 ሬክቴር ስኬል የተመዘገበው የቫልዲቪያ ርዕደ መሬት ሲሆን፣ ለ1,655 ሰዎች ሞት እና ሁለት ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።
በሩሲያ ካምቻትካ ባሕረ ሰርጥ አቅራቢያ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ2011 ወዲህ እጅግ በጣም ኃይለኛ ነው። ይህ ርዕደ መሬት በዚያ ዓመት በጃፓን ግሬት ቶሆኩ የተባለ ርዕደ መሬት፣ እርሱን ተከትሎም ሱናሚ እና ፉኩሺማ ላይ የኒውክሌር አደጋ አስከትሏል።
በአውሮፓውያኑ 1952 በካምቻትካ ባሕረ ገብ መሬት አቅራቢያ ተመሳሳይ የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተ ሲሆን መጠኑም በሬክተር ስኬል 9 ነበር።
"በሃዋይ ላይ የተከሰተ ግዙፍ ሱናሚ ያስነሳ ሲሆን፣ ከ1ሚሊዮን ዶላር በላይ ጉዳት አስከትሏል" ይላል የዩናይትድ ስቴትስ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ።
ባለፈው ሳምንት ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በፊት፣ በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱት በአውሮፓውያኑ 2010 በቺሊ የባሕር ዳርቻ 8.8 መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ እና በ1906 በኢኳዶር የተከሰቱት ናቸው።
እስካሁን ምን መዘዝ አስከትሏል?
እንደ የአካባቢው ባለሥልጣናት ገለጻ የመሬት መንቀጥቀጡ ከተከሰተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ 4 ሜትር ከፍታ ያለው ሞገድ ከባሕሩ ላይ ተነስቶ ወደቡን እና በሩሲያ ሰቬሮ ኩሪልስክ ከተማ የሚገኘውን የዓሣ ማቀነባበሪያ ተቋም አጥለቅልቋል።
በጃፓን 1.3 ሜትር ከፍታ ያለው የሱናሚ ማዕበል በሰሜናዊው ኢዌት ግዛት መድረሱን የአገሪቱ የአየር ሁኔታ ኤጀንሲ የገለጸ ሲሆን፣ የሱናሚ ማዕበል በአሜሪካ ሃዋይ እና ካሊፎርኒያ ግዛቶች የባሕር ዳርቻም ደርሷል።
የሱናሚ ማዕበል ማስጠንቀቂያዎቹ ግን በጃፓን፣በሩሲያ እና በሃዋይ ግዛቶች ብቻ የተወሰኑ እንዲሆኑ ተደርገዋል።
የሱናሚ ማስጠንቀቂያው በእነዚህ አካባቢዎች ብቻ እንዲወሰን ከመደረጉ በፊት ግን በጃፓን ብቻ 1.9 ሚሊዮን ሰዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡ ተነግሯቸው ነበር።
በኮሎምቢያ እና በኒውዚላንድ ግን ቤታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ የተነገራቸው ሰዎች ትዕዛዙ እንደሚቆይ ተገልጾላቸዋል።
በርካታ የሱናሚ ማስጠንቀቂያዎች እና ምክሮች በሰሜን እና በደቡብ አሜሪካ፣ በኦሺኒያ እና በእስያ ክፍሎች አሁንም አሉ።
ከአላስካ እስከ ቶንጋ ያሉ በርካታ ማስጠንቀቂያዎች አሁን እንዲነሱ ተደርገዋል። ባለሥልጣናቱ የጠረፍ አካባቢዎችን በቅርበት መከታተላቸውን ቀጥለዋል።
ተመሳሳይ መጠን ካላቸው ያለፉ ርዕደ መሬቶች፣ የሱናሚ ምልከታ ዘገባዎች ላይ በመመሥረት ከፍተኛ የሱናሚ ሁኔታ ቢያንስ ለአንድ ቀን እንደሚቆይ ባለሥልጣናት ይገምታሉ።
ርዕደ መሬቶች ለምን ሱናሚዎች ይፈጥራሉ?
የምድር ተፈጥሯዊ አወቃቀር 'ቴክቶኒክ ፕሌትስ' ተብለው በሚለዩ የተለያዩ ክፍሎች ባሏቸው ንብርብሮች የተከፋፈለ ነው።
እነዚህ 'ፕሌቶች' (ንብርብሮች) በጣም በዝግታ ይንቀሳቀሳሉ፤ ምናልባትም በዓመት ጥቂት ሴንቲ ሜትር ብቻ፣ የእጃችን ጥፍር ከሚያድግበት ፍጥነት ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልክ ነው።
እርስ በርስ ሲቃረኑ ወይም ወደ አንዱ አቅጣጫ ሲሄዱ፣ የፕሌቶቹ ክፍሎች "ሊጣበቁ" ይችላሉ፣ እና ያን ጊዜ ቀስ በቀስ ውጥረት ይጨምራል።
ውሎ አድሮ፣ ይህ ውጥረት በጣም እየጠነከረ ይሄዳል፤ እና 'ፕሌቶቹ' ይንሸራተታሉ ወይም ወደ ቦታቸው ይመለሳሉ።
ይህ በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት የሚያጋጥመውን ከፍተኛ መጠን ያለውን ኃይል ይለቅቃል።
ይህ ከውቅያኖስ በታች ከተከሰተ እንቅስቃሴው በሁሉም አቅጣጫዎች ውሃን ከቦታው በከፍተኛ ኃይል እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል። ከዚያም በሱናሚ መልክ ወደ ባሕር ዳርቻ ሊሄድ ይችላል።
በሃዋይ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ እና የቴክቶኒክ ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ሔለን ጃኒስዝቭስኪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ለሱናሚ ሞገዶች ጥሩ ማሳያ በጄት አውሮፕላን ፍጥነት መጓዙ ነው።"
ስለዚህ፣ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በአውሮፕላን ለመጓዝ ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ ካሰቡ፣ የሱናሚ ማዕበል የመሬት መንቀጥቀጡ ከተከሰተበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመጓዝ የሚፈጅበት ተመሳሳይ ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ።
ሁሉም የመሬት መንቀጥቀጥ ሱናሚ ያስከትላል?
በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የውቅያኖስ እና የከባቢ አየር አስተዳደር (NOAA) መሠረት "በአጠቃላይ የመሬት መንቀጥቀጥ አደገኛ የሩቅ ሱናሚ ለመፍጠር ከ8.0 ሬክቴር ስኬል መጠን በላይ መሆን አለበት።"
"የውቅያኖስ ወለል እንቅስቃሴ መጠን፣ የመሬት መንቀጥቀጡ የሚከሰትበት አካባቢ ስፋት እና ከመሬት መንቀጥቀጡ በላይ ያለው የውሃ ጥልቀት ለሱናሚው መጠን አስፈላጊ ነገሮች ናቸው" ይላል።
በብሔራዊ የውቅያኖስ እና የከባቢ አየር አስተዳደር መሠረት አብዛኞቹ ሱናሚዎች የሚመነጩት ከ7.0 በላይ በሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ከውቅያኖስ በታች ወይም በጣም ቅርብ በሆነ እና ከምድር ወለል በታች ከ100 ኪሎ ሜትር በታች ነው።
በዓለም አቀፍ ታሪካዊ ሱናሚ መረጃ ቋት ውስጥ አብዛኞቹ ሱናሚዎች (89 በመቶ የሚሆኑት) የተፈጠሩት በትልቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በተፈጠረ የመሬት መንሸራተት ነው።