በተቃውሞ በምትናጠው ሚየንማር አን ሳን ሱቺ ተጨማሪ ክስ ቀረበባቸው

አን ሳን ሱቺ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከስልጣን በኃይል የተገረሰሱትና በእስር ላይ የሚገኙት የሚየንማር መሪ አን ሳን ሱቺ አዲስ ክስ ቀርቦባቸዋል።

በትናንትናው ዕለት በበይነ መረብ አማካኝነት ቀርበው ክሳቸው በቪዲዮ ተነቦላቸዋል።

በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ህገ -ወጥ የመገናኛ ዘዴዎች እንደ ዋኪ ቶኪ በመያዝ ክስ ተከሰው የነበረ ሲሆን በትናንትናው ዕለት ደግሞ የአገሪቱን የተፈጥሮ አደጋዎች ህግ በመጣስ ወንጀል ተከሰዋል።

ምንም እንኳን የተፈጥሮ አደጋዎች ህግ ጥሰዋል ቢባልም ዝርዝር መረጃ እስካሁን አልቀረበም።

አገሪቷ መፈንቅለ መንግሥት ከተከሰተባት እለት ጀምሮ በአደባባይ ተቃውሞዎች እየተናጠች ሲሆን ጦሩም አዲስ ምርጫ እንደሚያካሂድ ቃል ገብቷል።

ሆኖም ተቃዋሚዎቹ አን ሳን ሱቺን ጨምሮ በምርጫ ያሸነፉ መሪዎቻችን ይፈቱ በሚለው ጥያቄ ፀንተውበታል።

በባለፉት ሳምንታት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የአደባባይ ተቃውሞ አንስተዋል።ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መመለስ አለበት በማለት ጥሪያቸውን እያሰሙ ነው።

ተቃዋሚዎቹ በቀድሞዋ በርማ በአሁኗ ሚየንማር የተላለፈውን የስብሰባ እግድ በመጣስ ነው ተቃውሟቸውን እየገለፁ ያሉት።

ስልጣን በኃይል የተቆጣጠረው ጦር ያንጎንና ማንዳላይ በመሳሰሉ ከተሞች ከአምስት ሰዎች በላይ መሰብሰብ አይቻልም የሚል ትዕዛዝ ከማስተላለፍ በተጨማሪ የሰዓት እላፊ አዋጅ ጥሏል።

ስልጣን በኃይል ከጨበጠ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጦሩ ባካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ቃለ አቀባዩ ብርጋዲየር ጄነራል ዛው ሚን ቱን እንዳሉት ወታደራዊው ኃይል በስልጣን ለረዥም ጊዜ እንደማይቆይ ተናግረዋል።

በሚመጣው ምርጫ "ለአሸናፊው ፓርቲ ስልጣን እናስረክባለን" ሲሉ ቃል ገብተዋል።

ነገር ግን ምርጫው መቼ እንደሚካሄድ ትክክለኛ ቀን አልተሰጠም።

በዚሁ ቀን እንዲሁ በርካታ የጦሩ አባላት በተደጋጋሚ እንደሚናገሩት ቃለ አቀባዩም አገሪቱ ባለፈው ህዳር ያደረገችው ምርጫ የተጭበረበረ ነው ብለዋል። ለዚህ ንግግራቸው አባሪ አቅርበው ያደረጉት መረጃ የለም።

የአን ሳን ሱቺ ፓርቲ ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ ፓርቲ በከፍተኛ ድምፅ አሸንፎ መንግሥት መመስረት የቻለ ሲሆን ጦሩ በበኩሉ ተጭበርብሯል ከማለት አልፎ ለመፈንቅለ መንግሥቱንም እንደ ምክንያትነት ያቀርበዋል።

የአን ሳን ሱቺን ክስ አስመልክቶ ብሪታንያና አሜሪካ ትችታቸውን ሰንዝረዋል። የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ክሱ "የተፈጠረና ሰብዓዊ መብቷን የሚጥስ" ያሉት ሲሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃለ አቀባይ በበኩላቸው "የሚረብሽ ነው" ብለውታል።

በቅርቡም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሚየንማር መፈንቅለ መንግሥት አመራሮች ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችላቸውን ትእዛዝ አስተላልፈዋል።

ጆ ባይደን ያሳለፉት እቀባ የጦሩ አመራሮች፣ ቤተሰቦቻቸውና ከነሱ ጋር የንግድ ሽርኪያ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉት ሁሉ ላይ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ በአሜሪካ ተቀማጭ የሆነ የሚየንማር 1 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ጦሩ እንዳያገኘው ለማድረግ እግድ ለመጣል በሂደት ላይ ነው ተብሏል።

ጆ ባይደን መፈንቅለ መንግሥቱ እንዲቀለበስና መሪዋን አንግ ሳን ሱቺን ጨምሮ በእስር ላይ ያሉት የሲቪል አመራሮች እንዲፈቱ ጠይዋል።