አሜሪካ በሚየንማር መፈንቅለ መንግሥት መሪዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሚየንማር መፈንቅለ መንግሥት አመራሮች ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችላቸውን ትእዛዝ አስተላልፈዋል።
ጆ ባይደን ያሳለፉት እቀባ የጦሩ አመራሮች፣ ቤተሰቦቻቸውና ከነሱ ጋር የንግድ ሽርኪያ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉት ሁሉ ላይ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በአሜሪካ ተቀማጭ የሆነ የሚየንማር 1 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ጦሩ እንዳያገኘው ለማድረግ እግድ ለመጣል በሂደት ላይ ነው ተብሏል።
መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ አንዲት ግለሰብ ጭንቅላቷ ላይ በጥይት ተመትታ በመዲናዋ ናይ ፓይ ታው በሚገኝ ሆስፒታል ህይወቷ አልፏል።
በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ፖሊስ ተቃዋሚዎችን ለመበተን ውሃ፣ አስለቃሽ ጋዝና ጥይት በመተኮስ በሚሞክርበት ወቅት ነው ሴትዮዋ የቆሰለችው።
ግለሰቧ በጥይት እንደተመታች ማስረጃ መኖሩን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።
በባለፈው ሳምንት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡትን የአንግ ሳን ሱቺ መንግሥት በኃይል መገርሰሱን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የአደባባይ ተቃውሞ አንስተዋል።
ተቃዋሚዎቹ በቀድሞዋ በርማ በአሁኗ ሚየንማር የተላለፈውን የስብሰባ እግድ በመጣስ ነው ተቃውሟቸውን እየገለፁ ያሉት።
ስልጣን በኃይል የተቆጣጠረው ጦር ያንጎንና ማንዳላይ በመሳሰሉ ከተሞች ከአምስት ሰዎች በላይ መሰብሰብ አይቻልም የሚል ትዕዛዝ ከማስተላለፍ በተጨማሪ የሰዓት እላፊ አዋጅ ጥሏል።
ሆኖም ተቃዋሚዎቹ ሳምነት ባስቆጠረው የጎዳና ላይ ሰልፍ በኃይል የተገረሰሱትን አን ሳን ሱቺን ከስልጣን መወገድ እየተቃወሙ ነው።
ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መመለስ አለበት በማለት ጥሪያቸውን እያሰሙ ነው።
ፖሊስ ተቃዋሚዎቹን ለመበተን የሚጠቀመውን ኃይል በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ከፍተኛ የአካል ጉዳቶች ሪፖርት ቢደረጉም ሞቶች አልተከሰቱም ተብሏል።
ባይደን ሚየንማር ምን እንድታደርግ ነው የሚጠይቁት?
ጆ ባይደን መፈንቅለ መንግሥቱ እንዲቀለበስና መሪዋን አንግ ሳን ሱቺን ጨምሮ በእስር ላይ ያሉት የሲቪል አመራሮች እንዲፈቱ ጠይዋል።
"የሚየንማር ዜጎች የተቃውሞ ድምፃቸውን እያሰሙ ነው፤ አለምም እየተመለከተ ነው" በማለት የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ አስፈላጊም ከሆነ ሌሎች እርምጃዎች እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል።
"ተቃውሞዎች በተቀጣጠሉበት በአሁኑ ወቅት ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን የሚጠይቁ ዜጎች ላይ ኃይል መጠቀም ተቀባይነት የለውም። ይህንንም ሁኔታ በዝምታ አናየውም" ብለዋል።
አስተዳደራቸው ማዕቀቡ የሚጣልባቸውን የመጀመሪያ ዙር የጦር አመራሮች ዝርዝር በዚህም ሳምንት ያወጣል ተብሏል። ነገር ግን አንዳንዶቹ የጦር አመራሮች ከሮሂንጃ ሙስሊሞች ጭፍጨፋ ጋር ተያያዞ በጥቁር መዝገብ ውስጥ ያሉ ናቸው።
"በሚየንማር ወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እንጥላለን። የሚየንማርን መንግሥት የሚረዳ ማንኛውንም የአሜሪካ ንብረት ላይ እግድ እናሳልፋለን። ለአገሪቷ የጤና ስርአት፣ ሲቪል ሶሳይቲ ቡድኖችና የሚየንማርን ህዝብ በቀጥታ የሚጠቅሙ ድጋፎችን ከማድረግ ወደኋላ አንልም" ብለዋል።
በባለፈው ወር ስልጣን የተረከቡት አዲሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይህ የመጀመሪያ ማዕቀባቸው ነው።












