የሚየንማር የአደባባይ ተቃውሞ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከሰሞኑ መፈንቅለ መንግሥት በተነሳባት ሚየንማር ነዋሪዎቿ ተቃውሟቸውን ለመግለፅ አደባባይ ላይ መውጣታቸውን ተከትሎ ፖሊስ ውሃ በመርጨት ሰልፈኞቹን ሊበትን ሞክሯል።
ተቃዋሚዎቹ አደባባይ ላይ የወጡት በርካታ ሰዎች መሰብሰብ የሚከለክለውን እግድ በመተላለፍ ነው።
ስልጣን በኃይል የተቆጣጠረው ጦር ያንጎንና ማንዳላይ በመሳሰሉ ከተሞች ከአምስት ሰዎች በላይ መሰብሰብ አይቻልም የሚል ትዕዛዝ ከማስተላለፍ በተጨማሪ የሰዓት እላፊ አዋጅ ጥሏል።
ሆኖም ተቃዋሚዎቹ አራተኛ ቀን ባስቆጠረው የጎዳና ላይ ሰልፍ በኃይል የተገረሰሱትን አን ሳን ሱቺን ከስልጣን መወገድ እየተቃወሙ ነው።
ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መመለስ አለበት በማለት ጥሪያቸውን እያሰሙ ነው።
የአገሪቱ የመንግሥት ሚዲያ በበኩሉ ህግ የማያከብሩ ብሎ በጠራቸው እነዚህ ተቃዋሚዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ቢያስጠነቅቅም ሰልፈኞቹ ፍንክች አላሉም።
በባጎ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተቃዋሚዎች ውሃ የሚረጩ ፖሊሶችን ተጋፍጠዋል።
ሚየንማር ናው በተባለው የዜና ወኪል መሰረት በመዲናዋ ናይ ፓይ ታው ፖሊስ ተቃዋሚዎችን ለመበተን ውሃ በመርጨቱ ጉዳት የደረሰባቸው አሉ ብሏል።
ኢንሴይንና ማናዳላይ በመሳሰሉ ከተሞች እንዲሁ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተቃዋሚዎች መሰብሰባቸውን ከቦታው የወጡ ፎቶዎች ያሳያሉ።
"ማስጠንቀቂያቸው አያስፈራንም። ለዚያም ነው ዛሬም ለተቃውሞ የመጣነው። ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ስልጣን መቆጣጠራቸውን አንቀበለውም። ወታደራዊ አምባገነንነትን በጭራሽ አንፈልግም" በማለት ቲይን ዊን ሶ የተባሉ መምህር ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
በአገሪቱ ህዝባዊ ተቃውሞ እየተካሄደ ሲሆን በተለያዩ ከተሞች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን ለመበተን ፖሊስ ውሃ የተጠቀመው ለመጀመሪያ ጊዜ በትናንትናው እለት ነው።
የጦሩ መሪ ሚን አንግ ሂላይንግ ማንኛውም ሰው "ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም" በማለት ቢያስጠነቅቁም ተቃወሚዎቹን በቀጥታ ከማስፈራራት ተቆጥበዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ















