በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣናቸውን ያጡት የኖቤል ሎውሬት አን ሳን ሱ ቺ ማን ናቸው?

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦባማና አንግ ሳን ሱቺ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በአንድ ወቅት የሰብአዊ መብትና የዲሞክራሲ ባንዲራ ሆነው ይታዩ ነበር፡፡ አሁን ግን በብዙ ተቋማት ዓይንዎትን ላፈር ተብለዋል፤ አን ሳን ሱ ቺ፡፡

ከሳምንት በፊት በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣናቸውን አጥተዋል፡፡ አሁን በቁም እስር ላይ ናቸው፡፡

ከስማቸው አወዛጋቢነት እስከ አገሪቱ ትክክለኛ የስም አጠራር ድረስ የቀድሞዋ በርማ የአሁኗ ሚየንማር፣ የቀድሞዋ የሰብአዊ መብት እመቤት፣ የአሁኗ እስረኛ የሰሞኑ የሚዲያ ዐቢይ ጉዳይ ሆነዋል፡፡

በእርግጥ የሴትዮዋ ‹ሌጋሲ› በትክክል ምንድነው? በሚለው ጉዳይ ሚዲያዎችና ተቋማት ተስማምተው አያውቁም፡፡

ለመሆኑ ኦን ሳን ሱ ቺ ማን ናቸው?

አን ሳን ሱ ቺ አባታቸው የበርማ የነጻነት አባት የሚባሉት የጄኔራል ኦን ሳን ሴት ልጅ ናቸው፡፡

ታላቋ ብሪታኒያ በርማን (በአዲሱ ስሟ ሚየንማር) ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል ጊዜ በቅኝ ገዝታታለች፡፡

ጄኔራል ኦን ሰን ለበርማ ነጻነት ተዋድቀዋል፡፡ የተገደሉትም በ1947 በተቀናቃኞቻቸው ነበር፡፡ ያን ጊዜ ሳን ሱ ቺ ገና 2 ዓመቷ ነበር፡፡ አን ሳን ሱ ቺ በሰኔ 19፣ 1945 ነበር የተወለዱት፡፡

ኦን ሳን ሱ ቺ በ1960ዎቹ መጀመርያ ከእናታቸው ዳው ኪን ኬዪ ጋር ወደ ሕንድ ሄዱ፡፡ እናታቸው በደልሂ የበርማ አምባሳደር ተደርገው በመሾማቸው ነበር ወደዚያ ያቀኑት፡፡

ሕንድ አራት ዓመት ከኖሩ በኋላ ወደ ታላቋ ብሪታኒያ በማቅናት በሥመጥሩ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፍልስፍናን፣ ፖለቲካንና ምጣኔ ሀብትን አጥንተዋል፡፡

አን ሳን ሱ ቺ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ሳሉ የወደፊት ባለቤታቸው ጋር ተገናኙ፡፡ እንግሊዛዊው ባለቤታቸው ማይክል አሪስ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ነበሩ፡፡ አሁን በሕይወት የሉም፡፡

ኦን ሳን ሱ ቺ ከትምህርት በኋላ በቡታን እና በጃፓን በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ታላቋ ብሪታኒያ በመሄድ ጎጆ መሥርተው አሌክሳንደርና ኪም የሚባሉ ልጆችን አፍርተዋል፡፡

በ1988 ከታላቋ ብሪታኒያ ወደ ሚየንማር ዋና ከተማ ያንጎን ሲመለሱ በጠና ታመው የነበሩትን እናታቸውን ለማስታመም ነበር፡፡

የአጋጣሚ ነገር ሆኖ በበዚያ ወቅት በሚየንማር በርካታ የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን ያነሱ ወጣቶች አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ያስነሱበት ጊዜ ነበር፡፡

ተቃዋሚዎቹ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ የቡድሀ መነኮሳት፣ የቢሮ ሰራተኞችና ተማሪዎችም ይገኙበት ነበር፡፡

ይህን ተቃውሞ ተከትሎ አን ሳን ሱ ቺ ጠቅልለው በሚየንማር መኖር ጀመሩ፡፡

አን ሳን ሱቺ ከቀድሞ ባለቤታቸው ጋር በለንደን

የፎቶው ባለመብት, Aris Family Collection/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አን ሳን ሱቺ ከቀድሞ ባለቤታቸው ጋር በለንደን

ከ2 ዓመት በኋላ በ1990 አዲስ በተመሠረተው የናሽናል ሊግ ፓርቲ ውስጥ ገብተው ተቃውሞ ውስጥ በቀጥታ መሳተፍ ጀመሩ፡፡ በአካባቢ ምርጫ ተወዳድረውም አሸነፉ፡፡

በከፍተኛ ድምጽ የኦን ሳን ሱ ቺ በምርጫ ማሸነፍ ያስቆጣው ወታደራዊው መንግሥት ሴትዮዋን ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት በቁም እስር አስቀመጣቸው፡፡

በ1991 ኦን ሳን ሱ ቺ በቁም እስር ላይ ሳሉ የኖቤል ሽልማትን አሸነፉ፡፡ ይህም ወታደራዊውን መንግሥት በይበልጥ አስቆጣ፡፡

በ2010 ኦን ሳን ሱ ቺ ከቁም እስር ነጻ ተባሉ፡፡

በ2012 አን ሳን ሱ ቺና ፓርቲያቸው በአካባቢ ምርጫ እንዲሳተፉ ወታደራዊው መንግሥት ፈቀደ፡፡

በ2015 የብሔራዊ ሊግ ለዲሞክራሲ (NLD) ፓርቲያቸው ለመጀመርያ ጊዜ በተደረገ ከፍተኛ ፉክክር በታየበት ምርጫ አሸነፈ፡፡

አን ሳን ሱ ቺ በሚየንማር የሮሒንጋ ሙስሊሞች ላይ ወታደሩ ያደረሰውን ግፍና ጭፍጨፋ ለማውገዝ አለመፍቀዳቸው በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ቁጣን ቀሰቀሰ፡፡ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የሮሒንጋ ሙስሊሞች ከሚየንማር ሞትን ሽሽት ወደ ባንግላዴሽ ተሰደዋል፡፡

በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ክብራቸው ዝቅ ይበል እንጂ አን ሳን ሱ ቺ በአገራቸው ቡድሀዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ናቸው፡፡

አን ሳን ሱ ቺ በ2015 የተደረገውን ምርጫ አሸንፈው መንግሥት ቢመሠርቱም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት መሆን ግን አልተፈቀደላቸውም፡፡ ይፋዊ ሥልጣናቸው ‹የመንግሥት የበላይ ጠባቂ› ወይም ስቴት ካውንስለርነት ነው፡፡

ይህም የሆነው ያፈሯቸው ልጆች የውጭ ዜግነት ስላላቸው ነው፡፡ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሚስተር ዊ ቢሆኑም አን ሳን ሱ ቺ ግን በውስጥ ታዋቂነት (de facto) የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሆነው ይወሰዳሉ፡፡

ስቴት ካውንስል የሚባለው ሹመት የተፈጠረው አን ሳን ሱ ቺ ሕጋዊ ፕሬዝዳንት መሆን ስለማይችሉ ነው፡፡ ሆኖም በፖለቲካ ሥልጣን ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ያህል ቁልፍ ቦታ ነው፡፡

አን ሳን ሱ ቺ ይህን ሥልጣን ከመቆናጠጣቸው በፊት ለአጫጭር ጊዜም ቢሆን የኢነርጂ ሚኒስትር፣ የትምህርት ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ማለትም 2020 አን ሳን ሱ ቺ እና ፓርቲያቸው ምርጫ ማሸነፍ ችሎ ነበር፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉትም አዲሱን መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና በሚሉበት ሰዓት ነው፡፡

በ2021 የዛሬ ሳምንት አካባቢ የተወካዮች ምክር ቤት ሸንጎ አዲስ የሥራ ዘመን ስብሰባ በሚጀምርበት ቀን አን ሳን ሱ ቺ በድጋሚ በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

አን ሳን ሱ ቺ አሁን የ76 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ናቸው፡፡