የሚየንማር ወታደራዊ መሪዎች "አገሪቷን ለማረጋጋት" በሚል ፌስቡክን አገዱ

ተቃዋሚዎች በሚየንማር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከቀናት በፊት የሚየንማርን መንግሥት በኃይል የገረሰሰው ወታደራዊ ኃይል የማህበራዊ ሚዲያውን ፌስቡክ አግዶታል።

ወታደራዊ መሪዎቹ ፌስቡክን ለማገድ ምክንያት ነው ያሉት "አገሪቷ እንድትረጋጋ" ለማድረግ ነው ብለዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የተነሳውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ በርካታ የአገሪቷ ዜጎች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ያሉት በፌስቡክ ነው።

ፌስቡክ ለተቃውሞው አጋርም ሆኗል እየተባለ ነው።

ከዚህ ሰላማዊ አመፅ ጋር ተያያይዞ የአገሪቱ ምክር ቤት አባላት ከመዲናዋ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቶች ወደ ውጭ አንወጣም በማለት ተቃውሟቸውን እያሳዩ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በያንጎን ከተማ እንዲሁ ነዋሪዎች ከበሮ በመደብደብ የሰላማዊ አመፁን እንዳጠናከሩ እየተዘገበ ነው።

የፌስቡክ ሚና ምንድን ነው?

የአገሪቱ ኮሚዩኒኬሽንና መረጃ ሚኒስቴር እንዳሳወቀው ፌስቡክ ለቀናት ያህል ዝግ እንደሚሆን ነው።

ነገር ግን ሚኒስቴሩ ውሳኔውን ካሳለፈ በኋላ ቢቢሲ ባገኘው መረጃ መሰረት አንዳንዶች ፌስቡክን እየተጠቀሙ እንደነበር ነው።

በያንጎን የጉዞና የአስጎብኝ ድርጅት ያለው አንቶኒ አንግ ለቢቢሲ እንደተናገረው በዋይፋይ ፌስቡክን መጠቀም እንደሚችልና በዳታ ብቻ እንደታገደ ተናግሯል።

በርካቶችም ፌስቡክን መጠቀም ያስችላቸው ዘንድ አማራጭ ቪኢኤን እየጫኑ እንደሆነም አስረድቷል።

ነገር ግን ይህንን ከተናገረ ከሰዓታት በኋላ ሙሉ በሙሉ ፌስ ቡክ ተዘግቷል።

በርካቶችም ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን የሚጥስ ነው በማለት እየተቹት ነው።

ከሚየንማር 54 ሚሊዮን ዜጎች መካከል ግማሹ ፌስቡክን የሚጠቀሙ ሲሆን በተለይ በዚህ ወቅትም የአገሪቱ በርካታ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና አቀንቃኞች መፈንቅለ መንግሥቱን ለመቃወም የፌስቡክ ገፆችን በመፍጠር ድምፃቸውን እያሰሙ ነበር።

ፌስቡክ መታገዱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ "ባለስልጣናቱ እግዱን እንዲያነሱና የሚየንማር ዜጎች ከቤተሰቦቻቸው፣ ከወዳጅ፣ ዘመድና ጓደኞቻቸው ጋር በነፃነት መረጃ እንዲለዋወጡና እንዲገናኙ ማድረግ አለባቸው" በማለት ኩባንያው ጠይቋል።

ቴሌኖር ሚየንማር የተባለው የቴሌኮም ኩባንያ በበኩሉ ፌስቡክን እንዲያግድ የተሰጠውን የመንግሥት ትዕዛዝ ተግባራዊ ቢያደርግም ይህ ሁኔታ የሰብዓዊ መብትን የሚጥስ ነው በማለት በመግለጫው አውጥቷል።