ሚየንማር፡ በመፈንቅለ መንግሥት የተፈነገሉት የሚየንማሯ ፕሬዝዳንት ሳን ሱ ቺ ተከሰሱ

ሳን ሱ ቺ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በመፈንቅለ መንግሥት የተፈነገሉት የሚየንማሯ ፕሬዝዳንት ክስ ተመሰረተባቸው።

ሰኞ ዕለት መፈንቅለ መንግሥት በተደረገባቸው የሚየንማር ፕሬዝዳንት ሳን ሱ ቺ ላይ ፖሊስ በርከት ያሉ የክስ መዝገቦችን ከፍቶባቸዋል።

የፖሊስ መዝገብ እንደሚያሳየው ከሆነ ፕሬዝዳንቷ እስከ የካቲት ስምንት ድረስ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ይቆያሉ ተብሏል። ሕጋዊ ያልሆኑ የወጭ እና ገቢ ንግዶችን እንዲሁም በሕገ ወጥ መንገድ የኮሚዩኒኬሽን ንብረቶች ባለቤት መሆን የሚሉት ከክሶቹ መካከል ናቸው።

እስካሁን ፕሬዝዳንቷ የት እንዳሉ አይታወቅም፤ ነገር ግን በመዲናዋ ናይ ፒይ ታው ውስጥ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል።

ከስልጣን የተወገዱት ፕሬዝዳንት ዊን ሚንትም ተከሰዋል። እርሳቸው የተከሰሱበት ወንጀል ደግሞ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተጣለውን የመሰብሰብ እገዳ በመተላለፍ ነው ተብሏል።

በመሆኑም ለሁለት ሳምንታት ያክል በፖሊስ ቁጥጥር ውስጥ ይቆያሉ ብሏል። ሁለታቸውም ግን መፈንቅለ መንግሥቱ ከተካሄደ ጊዜ ጀምሮ ድምጻቸው አልተሰማም።

በሚን አውንግ ህላይንግ የተመራው ወታደራዊው መፈንቅለ መንግሥቱ 11 አባላትን በማዋቀር ለአንድ ዓመት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የአስተዳደር ሥራውን ጀምሯል።

ወታደራዊው ጁንታ ባለፈው ህዳር ወር የተካሄደውን ምርጫ የተጭበረበረ ነው በማለት መፈንቅለ መንግሥቱን ተቀባይነት ለማስገኘት እየጣረ ነው።

አሁን ላይ በፖሊስ የቀረቡት የክስ ዝርዝሮች የመጀመሪያና ለፍርድ ቤት የቀረቡ ሪፖርቶች ናቸው ተብሏል። በእዚህም የኮሚዩኒኬሽን መሳሪያዎችን በሕገ ወጥ መልኩ አስገብተው በቤታቸው ተገኝቷል የሚል ክስ በሳን ሱ ቺ ላይ ቀርቦባቸዋል።

እማኞችን ለመጠየቅ፣ መረጃ ለመጠየቅ እና ተከሳሿን ጠይቆ የሕግ ምክር ለማግኘት ሲባል በቁጥጥር ሥር መቆየታቸውን የክስ መዝገቡ አስረድቷል።

ዊን ሚይንት ደግሞ በብሔራዊ 'ዲዛስተር ማኔጅመንት' ሕግ የተከሰሱ ሲሆን፣ የቀረበባቸው ክስ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተጣለውን እገዳ በመጣስ ለምርጫ ቅስቀሳ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ስብሰባ አካሂደዋል የሚል ነው።