በርማ፡ በሚየንማር መፈንቅለ መንግሥት ተደረገ፤ ሳን ሱ ቺ ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በቀድሞዋ በርማ በአሁኗ ምያንማር ወታደሩ ሥልጣን መቆጣጠሩ ተሰምቷል።
ወታደሮች ሥልጣን መቆጣጠራቸውን ይፋ ያደረጉት የሲቪል መንግሥት አባላትን በቁጥጥር ሥር ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።
የኖቤል ተሸላሚዋ ኦንግ ሳን ሱ ቺ እና ሌሎች የፖለቲካ መሪዎች ተለቅመው ወዳልታወቀ ሥፍራ ተወስደዋል።
በሚየንማር በወታደሩ እና በሲቪሊያን አስተዳደሩ መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውጥረት ተከስቶ ነበር።
እነ ሳን ሱ ቺ ከመታሰራቸው በፊት የመንግሥት ቴሌቪዥን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ነበር።
ሚየንማር የዲሞክራሲያዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ እስከጀመረችበት 2011 ድረስ በጥብቅ ወታደራዊ መንግሥት ነበር ስትመራ የቆየችው።
ባለፈው ሕዳር በተደረገ ምርጫ የሳን ሱ ቺ ፓርቲ 'ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ' መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን የመቀመጫ ቁጥር ማግኘት ችሎ ነበር። ሆኖም ወታደሮቹ ምርጫው ተጭበርብሯል ሲሉ ቆይተዋል።
ዛሬ [ሰኞ] ወታደሮች የአገሪቱን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውና መሪያቸውም ኮማንደር ሚነ ኦንግ ሌይንግ መሆናቸው ተናግረዋል።
በርካታ ወታደሮች በአገሪቱ ዋና ከተማ ናይፒታው እና በሌላኛዋ ዋንኛ ከተማ ያንጎን ይታያሉ።
የሞባይልና ኢንተርኔ አገልግሎት እንዲሁም ስልክ በስፋት የተቋረጠባቸው ዋና ዋና ከተሞች ላይ ሲሆን የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ሥርጭት ለማድረስ እክል ገጥሞኛል በማለት ተቋርጧል።
በርካታ ወታደሮችም በተለያዩ ቦታዎች እየሄዱ የሲቪል አስተዳደሩ ሚኒስትሮች የነበሩ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር እንዳዋሉ ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።
የቢቢሲዋ የደቡብ ምሥራቅ ኢሲያ ወኪላችን እንዳለችው ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ያላትን ሳን ሱ ቺን የመሰሉ ፖለቲከኞችን ማሰር ትልቅ ውሳኔ ነው።
የሳን ሱ ቺ ፓርቲ ባለፈው ህዳር በተደረገ ምርጫ 83% መቀመጫ አሸንፎ ነበር። ይህም ለሳን ሱ ቺ መንግሥት ሕዝብ ይሁንታን መስጠቱን የሚያሳይ ተደርጎ ነበር የተወሰደው።
ይህ ምርጫ የወታደራዊ መንግሥት አስተዳደር ካበቃበት ከ2011 ወዲህ ሲካሄድ ለ2ኛ ጊዜ ነው።
ነገር ግን ይህን ምርጫ ወታደሩ ሳይቀበለው ቀርቶ ነበር።
ይህን ተከትሎም ምናልባት ወታደሩ መፈንቅለ መንግሥት ያደርግ ይሆናል የሚል ፍርሃት ነግሶ ቆይቶ ነበር።
ኦንግ ሳን ሱ ቺ ማን ናት?
ሳን ሱ ቺ የበርማ የነጻነት አባት የሚባሉት የጄኔራል ኦንግ ሳን ሴት ልጅ ናት።
አባቷ የተገደሉት እሷ ገና የ2 ዓመት ልጅ ሳለች ነበር። የተገደሉትም በርማ ከእንግሊዝ ነጻነቷን ከመቀዳጀቷ ጥቂት ቀደም ብሎ እንደነሱ አቆጣጠር በ1948 ነበር።
ሳን ሱ ቺ በአንድ ወቅት ለዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት ትልቅ ተምሳሌት ተደርጋ ነበር የምትታየው። ምክንያቱም ምሕረት አያውቁም ከሚባሉት የምያንማር ወታደራዊ ኃይሎች በተጻጻራሪ በመቆም በአገሪቱ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን በመታገል ረዥም ዓመታት አሳልፋለች።
ይህን ተከትሎም በ1991 የኖቤል የሰላም ሽልማትን ማሸነፍ ችላ ነበር።
ሽልማቱን ያሸነፈችውም በቁም እስር ላይ ሳለች ነበር።
ሳን ሱ ቺ ለ15 ዓመታት በእስር ከቆየች በኋላ በ2010 ነጻ ተደርጋለች።
በ25 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገ ምርጫም ፓርቲዋ ትልቅ ድል አግኝቶ ወደ ሥልጣን መምጣት ችላ ነበር።
ሆኖም የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ሳን ሱ ቺ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት እንድትሆን አይፈቅድም። ምክንያቱም ልጆቿ የውጭ ዜጎች ስለሆኑ ነው። በዚህም የተነሳ መንግሥትን የምትመራው ከጀርባ ሆና ነው።
ሳን ሱ ቺ አሁን 75 ዓመት ሆኗታል።
የሰላም ኖቤል አሸናፊ የነበረችው ሳን ሱ ቺ በአገሯ የሮሒንጋ ሙስሊሞች ላይ ለደረሰው ግፍና መከራ ቸልተኝነት በማሳየቷ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያገኘቻቸው ክብርና እውቅናዎችን ተነጥቃለች።
ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ሔግ ቀርባ ለዚህ ምላሽ እንድትሰጥ በተደረገበት ጊዜ በሮሒንጋ ሙስሊሞች ላይ የደረሰውን ግፍ ተገቢነቱን ለማሳየት መሞከሯ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰጥቷት የነበረውን ክብር የሚያጠለሽ ሆኖ ተገኝቷል።
ሆኖም በአገሯ ውስጥ ሳን ሱ ቺ በቡድሃ ብዙኃን ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት አላት።














