ኮሮናቫይረስ፡ በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ የኮቪድ ክትባትን የሚቃወሙ ሰልፈኞች ከፖሊስ ተጋጩ

ዶጀር ስታዲየም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካ፣ ካሊፎርኒያ ግዛት፣ ሎስ አንጀለስ ከተማ የኮቪድ ክትባት ውሸት ነው የሚሉ ቀኝ አክራሪዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል፡፡

ከፖሊስ ጋር የተጋጩት ክትባት እየተሰጠበት የሚገኘውን የዶገር ስታዲየም በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ሰልፈኞቹ ይህን የክትባት መስጠቱ ሂደት ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ያህል እንዲስተጓጎል አድርገዋል፡፡

ቁጥራቸው 50 የሚሆኑ የጸረ ክትባት አቀንቃኞች ስታዲየሙን ለማዘጋት የቻሉት መግቢያውን በመዝጋት ጭምር ነው፡፡

ክትባት ለማግኘት ሰልፍ ላይ የነበሩ በርካታ መኪኖች በነዚህ የክትባት ተቃዋሚዎች ምክንያት አገልግሎት ሳያገኙ ተመልሰዋል፡፡

ሰልፈኞቹ የኮቪድ ክትባት የተጭበረበረ ስለመሆኑ የሚያወሱ መፈክሮችን የያዙ ሲሆን ኅብረተሰቡን ‹አትከተቡ፤ እናንተ የቤተ ሙከራ አይጥ አይደላችሁም› እያሉ ሲቀሰቅሱ ታይተዋል፡፡

የሎስ አንጀለስ ታይምስ ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ ቀኝ አክራሪ ሰልፈኞቹ ለክትባት የተሰለፉ ሰዎችን ‹ ነፍሳችሁን አድኑ፣ የውሸት ሳይንስ መጫወቻ አትሁኑ እያሉ እየጮኹ ሲቀሰቅሱ ነበር፡፡

የክትባት መስጫውን ሰልፈኞቹ የተቆጣጠሩትም በአገሬው አቆጣጠር ከቀኑ 8 ሰዓመት ጀምሮ ነው፡፡

የሎስ አንጀለስ ፖሊስ በትዊተር እንዳስታወቀው ስታዲየሙ አልተዘጋም፤ ክትባቱ ቀጥሏል ብሏል፡፡

የካሊፎርኒያ ገዥ ጋቪን ኒውሰን በስታዲየሙ እየተሰጠ የነበረው የክትባት ዘመቻ በሰልፈኞች ለጊዜው ቢስተጓጎልም ወደ ሥራ ተመልሷል ብለዋል፡፡

ጀርማን ጃኩዝ የተባለና ክትባት ለማግኘት ሰልፍ ሲጠባበቅ የነበረ ዜጋ ለሎስ አንጀለስ ታይምስ ቁጣውን የገለጸ ሲሆን ‹‹ይህ የቀኝ አክራሪዎች ድርጊት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው› ብሏል፡፡

‹‹ለሳምንታት ክትባት ለማግኘት ስጠባበቅ ነበር፡፡ እኔ የጥርስ ሐኪም ነኝ፡፡ በሽተኞቼን ሳክም በጣም ተጠግቻቸው ነው፡፡ ከኮቪድ መጠበቅ እሻለሁ፡፡ ክትባቱ ያስፈልገኛል፡፡ ተህዋሲውን ለመከላከል ብቸኛው መንገድ ክትባት ነው›› ሲል ሐሳቡን አጋርቷል፡፡

በአመዛኙ የትራምፕ ደጋፊ የነበሩ እንደሆኑ የሚገመቱና ቀኝ አክራሪ የሆኑት ሰልፈኞች ከያዟቸው መፈክሮች አንዱ ‹‹ሲኤንኤን እያታለላችሁ ነው›› ይላል፡፡

ሌሎች መፈክሮች፣ ‹‹ጭምብላችሁን ቀዳዳችሁ ጣሉት››፣ ‹‹የሰው አይጥ አትሁኑ›› የሚሉ ይገኙበታል፡፡

ከአሜሪካ ግዛቶች ካሊፎርኒያ በተህዋሲው ክፉኛ ከተጠቁት ተርታ ትመደባለች፡፡ 40ሺ የግዛቲቱ ነዋሪዎች በኮቪድ ሞተዋል፡፡ 3 ሚሊዮኑ ተህዋሲው አለባቸው፡፡

በመላው አሜሪካ በኮቪድ ተህዋሲ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች በሚቀጥለው ወር ግማሽ ሚሊዮን እንደሚያልፍ ይጠበቃል፡፡