ቻይና 'ታይዋን ነጻነቷን ካወጀች' ጦርነት እንደምትከፍት አስጠነቀቀች

የታይዋን ሰንደቅ ዓላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታይዋን ነጻ አገር ለመሆን አንዳች ሙከራ ካደረገች ጦርነት እንደሚገጥማት ቻይና አስጠነቀቀች።

ከቻይና እንዲህ ጠንከር ያለ የጦርነት ማስጠንቀቂያ ሲመጣ ይህ ከረዥም ጊዜ በኋላ የመጀመርያው ነው።

ይህ ማስጠንቀቂያ የመጣው ቤጂንግ የጦር አውሮፕላኖችን ወደ ደሴቲቱ አካባቢ ካስጠጋችና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን የታይዋን ድንበር አካባቢ ማድረጓ ከተዘገበ ከቀናት በኋላ ነው።

ይህ ብቻም ሳይሆን ታይዋንና አሜሪካ አዲስና ጠንካራ ግንኙነት ለመጀመር ከተነጋገሩ በኋላ ቻይና ይህን ማለቷ አዲስ ስጋት ፈጥሯል።

አዲሱ የባይደን አስተዳደር ባለፈው ሳምንት ከታይዋን ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክር መግለጹ ይታወሳል።

ባለፈው ሐሙስ ዋሺንግተን ታይዋንን በመከላከያው ዘርፍ መደገፏን እንደምትቀጥል የሚገልጽ መግለጫ መውጣቱ አይዘነጋም።

ቻይና ታይዋንን እንዳመጸች አንዲት ግዛቷ አድርጋ ነው የምትመለከታት። ታይዋን ግን ራሷን እንደ አንድ ሉአላዊት አገር ነው የምትመለከተው።

የቻይና የመከላከያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዉ ኪን ሐሙስ ዕለት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ጠንከር ያለ ሐሳብ ሰንዝረዋል።

"ቆፍጠን ብለን መናገር የምንፈልገው ነገር ቢኖር ታይዋኖች በእሳት እንዳይጫወቱ ነው። እሳቱ ይበላቸዋል" ካሉ በኋላ "ታይዋን ነጻ አገር ልሁን ካለች የሚከተለው ጦርነት ነው" ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።

ቻይና በታይዋን አቅራቢያ እያደረገች ያለችው ወታደራዊ እንቅስቃሴንም "ትክክለኛ አካሄድ ነው፤ ብሔራዊ ሉአላዊነትንና ደኅንነትን ለማስጠበቅ የሚደረግ ነው፤ ይቀጥላል" ብለዋል የቻይና መከላከያ ሰራዊት ቃል አቀባይ።

አሜሪካ በበኩሏ ሐሙስ ማምሻውን ለዚህ የቻይና ዛቻ ምላሽ ሰጥታለች።

ይህ ከቻይና የሚነገረው ንግግር ጸብ አጫሪነት ነው፤ አሜሪካ ከታይዋን ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያቆምም አይደለም ብለዋል የፔንታገን ፕሬስ ሴክሪታሪ ጆን ኪርቢ።

አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ከቻይና በርካታ ቁርሾዎችን የማብረድ ሥራ እንደሚጠብቀው እየተነገረ ነው፤ ከዚህ ከታይዋን ጉዳይ ሌላ በቻይና ሙስሊሞች ላይ የሚፈጸመው ኢሰብአዊ ድርጊት፣ ከቻይና ጋር ያለ የንግድ ጦርነት፣ የሆንግ ኮንግ ጉዳይ ይጠቀሳሉ።

አሁን ደግሞ የታይዋን ጉዳይ መጨመሩ ለጆ ባይደን አዲስ ራስ ምታት ይሆናል ተብሏል።

ቻይናና ታይዋን የቻይና የእርስ በርስ ጦርነት በ1949 ከተደረገ ወዲህ የተለያየ መንግሥት ኖሯቸው ነው የቀጠሉት። ሆኖም ቤጂንግ ለረዥም ጊዜ የታይዋንን የውጭ ግንኙነት ለመቆጣጠር ትሞክራለች።

ሁለቱም በፓስፊክ አካባቢ ያላቸውን ተጽእኖ ለመጨመር ሲተጉ ነው የኖሩት።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በታይዋንና ቻይና መካከል ያለው ውጥረት እያየለ ሲሆን ቤጂንግ እስከአሁን ደሴቲቱን ወደራሷ በኃይል የመመለሱን ሐሳብ እርግፍ አድርጋ አልተወችውም።

ታይዋን እንደ ሉአላዊት አገር የሚቆጥሯት አገሮች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ሆኖም በዲሞክራሲ የተመረጠው የታይዋን መንግሥት ጠንካራ የንግድ እና ኢ መደበኛ ግንኙነቶችን ከበርካታ የዓለም አገራት ጋር ያካሄዳል።

እንደ ብዙዎቹ አገሮች ሁሉ አሜሪካ ይፋዊ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ከታይዋን ጋር የላትም። ሆኖም የታይዋን 'ሪሌሽን አክት' የሚባለው የቃል ኪዳን ስምምነት አሜሪካ ለታይዋን የመከላከያ ዘመናዊ መሳሪያዎችን እንድታስታጥቅ እና በታይዋን ላይ የሚቃጣ ማንኛውም አደጋን የአሜሪካ ትልቅ ጉዳይ ሆኖ እንዲቀጥል ተስማማታለች።