በሚየንማር የሰላማዊ አመፅ እንቅስቃሴ መቀጣጠሉ ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሰሞኑ በሚየንማር ወታደራዊው ኃይል መፈንቅለ መንግሥት ማንሳቱን ተከትሎ በአገሪቱ ሰላማዊ አመፅ ተቀጣጥሏል።
ጦሩ ስልጣን በኃይል መቆጣጠሩን የሚቃወሙ በርካቶች ሲሆኑ በተለይም መምህራንና ተማሪዎች ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው ተብሏል።
በትልቋ ከተማ ያንጎን በሚገኝ ዩኒቨርስቲ ተቃዋሚዎች በኃይል የተገረሰሱትና በእስር ላይ የሚገኙትን መሪ አንግ ሳን ሱ ቺ ስም እያነሱ መፈክር ሲያሰሙ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የፓርቲያቸውን ቀለም የሚወክል ቀይ ሪባን አድርገዋል።
ኦንግ ሳን ሱቺን ጨምሮ የአገሪቱ ባለስልጣናት በእስር ላይ ነው የሚገኙት።
በዛሬው ዕለት እንዲሁ የአገሪቱን ስልጣን ተቆጣጥሮ የነበረውን የኦንግ ሳን ሱ ቺ ፓርቲ ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ (ኤንኤልዲ) ፓርቲ ከፍተኛ አመራር በቁጥጥር ስር ውለዋል።
መፈንቅለ መንግሥት ከተከሰተበት ከሰኞ እለት ጀምሮ ለህዝብ ያልታዩት ኦንግ ሳን ሱ ቺ በቤት ውስጥ እስር እንደሚገኙ አንድ የፓርቲያቸው ባለስልጣን አስታውቋል።
የቀድሞዋ በርማ በመፈንቅለ መንግሥቱ ማግስት ፀጥታ ወሯት የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ሰላማዊ አመፆች ተቀጣጥለዋል ተብሏል።
በዛሬው ዕለት በመቶዎች የሚቆጠሩ መምህራንና ተማሪዎች በዳጎን ዩኒቨርስቲ ውጭ ሰብሰብ ብለው ሶስት ጣቶቻቸውን በማውጣት ምልክት እያሳዩ ነበር። የሶስት ጣት ምልክት የጭቆና አገዛዝን ለመቃወም በአካባቢው የሚጠቀሙበት ነው።
"የኛ ትውልድ በእንደዚህ አይነት አምባገነን ስርአት እንዲሰቃይ አንፈቅድም" በማለት ሚን ስትሁ የተሰኘች ተማሪ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግራለች።
ከዚህም በተጨማሪ በሚየንማር የተለያዩ ግዛቶች በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል። መፈንቅለ መንግሥቱ ከተነሳ በኋላ የዛሬው በህዝብ ቁጥርም ሆነ የተለያዩ ግዛቶችን በመሸፈን ትልልቅ ናቸው ተብሏል።
በያንጎን የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች በምሽትም ቢሆን ከቤታቸው አካባቢ ከበሮ፣ ቆርቆሮዎችን በመደብደብ፣ አብዮታዊ መዝሙሮችን በመዘመር ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው። በቀን እንዲሁ ባትሪ በማብራት የሰላማዊ አመፅ እንቅስቃሴያቸውን አቀጣጥለውታል።
የጤና ባለሙያዎች፣ መምህራንና የመንግሥት ሰራተኞች ሰልፎችን በማካሄድ፣ የስራ አድማ በመምታት እንዲሁም አንዳንዶች ቀይ ሪባን በማድረግ ህዝባዊ እምቢተኝነታቸውን እያሳዩ ነው።












