የኡጋንዳዊ አማፂ ቡድን አመራር የነበረው በጦር ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኡጋንዳው ሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ የተሰኘው አማፂ ቡድን አመራር ነበር የተባለው የቀድሞው ህፃን ወታደር ዶሚኒክ ኦንግዌን በጦር ወንጀሎች የአለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቶታል።
ታሪካዊ በተባለው የፍርድ ሂደት ዶሚኒክ ኦንግዌር ለአለም አቀፉ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ሆኖ በቀረበው አስገዳጅ እርግዝና የጥፋተኝነት ብያኔ ተላልፎበታል።
በነውጠኛነቱ በሚታወቀው የኡጋንዳው ሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ በአስፈሪነቱ ስሙ የሚጠራው ዶሚኒክ በአለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ሲቀርብ የመጀመሪያ ግለሰብ ነው።
በመሪው ላይ የቀረቡበት ክሶች በአውሮፓውያኑ 2004 የተፈናቀሉ ኡጋንዳውያን መጠለያ በሆኑ አራት ካምፖች ላይ ጥቃት አድርሷል በሚል ሲሆን ከቀረቡበት 70 የጦር ወንጀሎችና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀል ክሶች መካከል በ61ዱ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
ፍርድ ቤቱም ከ4ሺህ በላይ የተጠቂ እማኞችን ምስክርነት ሰምቷል።
እስካሁን ባለው የእስር ጊዜ ያልተበየነበት ቢሆንም የእድሜ ልክ እስራት ሊጠብቀው ይችላል ተብሏል።
በህፃንነቱ ለወታደርነት ተጠልፎ የአማፂው ቡደን አባል የሆነው ዶሚኒክ ክሱም በሚታይበት ወቅት ጥፋተኛና ተጠቂ ሆኖ መቅረቡ ለፍርድ ቤቱ ግራ አጋቢ ነበር ተብሏል።
በአማፂው ቡድን ተጠልፎ የህፃን ወታደር የሆነው ዶሚኒክ በኋላም በተለያዩ ማዕረጎች አልፎ የኃላፊው ጆሴፍ ኮኒ ምክትል ለመሆን በቅቶ ነበር።
የዶሚኒክ ጠበቆች ከሆኑት አንዱ ክሪስፐስ አይና ኦዶንጎ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረው ውሳኔው "እንደ ቦንብ ፍንዳታ ነው" ብለዋል።
የሂውማን ራይትስ ዋች አካል የሆነው አለም አቀፉ የፍትህ ፕሮግራም ዳይሬክተር ኤሊሱ ኬፕለር በውሳኔው ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።
"በሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ የተበየነ የመጀመሪያና ብቸኛው ውሳኔ በመሆኑ ወሳኝ ነው" በማለት መናገራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፐሬስ በዘገባው አስነብቧል።
ዶሚኒክ ኦንግዌን ማን ነው?
- ወደ ትምህርት ቤት እየሄደ ባለበት ወቅት በሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ ተጠለፈ
- የተለያዩ ማዕረጎችን አልፎ የጦር መሪ ሊሆን በቃ
- ባርነትን ጨምሮ በጦር ወንጀሎችና በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀም ወንጀል ተከሰሰ
- አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በአውሮፓውያኑ 2005 የእስር ትዕዛዝ አወጣበት
- አሜሪካ በ2013 ግለሰቡ ያለበትን ለሚጠቁምና ለሚያሳስር ሰው 5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እሰጣለሁ አለች
- በ2015 ከተያዘ በኋላ ለአይሲሲ ተላልፎ ተሰጠ። በ2021 በጦር ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ ተገኘ












