በጊኒ ኢቦላ ተቀስቅሶ ሦስት ሰዎች ሞቱ

በጊኒ ኢቦላ ተቀስቅሶ 3 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በጊኒ ኢቦላ ተቀስቅሶ 3 ሰዎች ሞቱ። ሌሎች አራት ሰዎች ደግሞ ተቅማጥ፣ ማስመለስና የመድማት ምልክቶችን እያሳዩ እንደሆነ ተነግሯል።

አራቱ ሰዎች እነዚህን ምልክቶች ማሳየት የጀመሩት የአንድ በኢቦላ የሞተችን ነርስ ቀብር ከታደሙ በኋላ ነበር።

ባለሥልጣናት አዲስ የተሰራ ክትባት በዓለም ጤና ድርጅት በኩል እንደሚገኝ እየተናገሩ ነው።

በፈረንጆቹ ከ2013 እስከ 2016 ብቻ በምዕራፍ አፍሪካ ኢቦላ ወረርሽኝ የ11ሺ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።

ወረርሽኙ ጊኒን ጨምሮ ጎረቤቶቿን ላይቤሪያንና ሴራሊዮንን በከፍተኛ ሁኔታ አጥቅቶ ነበር። ይህን ተከትሎም በርካታ ክትባቶች ተሞክረዋል። ክትባቶቹ ወረርሽኞቹን ለማቆም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ አገልግሎት ላይ ሲውሉ ነበር።

የዓለም ጤና ድርጅት የጊኒ ተወካይ አልፍሬድ ጆርጅ ኪ ዜርቦ "አስፈላጊውን ክትባት ለማቅረብ የዓለም ጤና ድርጅት ከመድኃኒት አምራቾች ጋር እየተነጋገረ ነው ብለዋል።

የኢቦላ ክትባት ለመጀመርያ ጊዜ በ2015 በጊኒ ሙከራ ተደርጎ ውጤት ማስገኘቱ ይታወሳል። ከክትባቱ ሌላ ታማሚው የመዳን እድሉን የሚጨምሩ መድኃኒቶች መፈብረካቸውም ይታወቃል።

አሁን በጊኒ የተቀሰቀሰው ኢቦላ በአንድ ጤና ጣቢያ ትሰራ የነበረች ነርስ ታማ ከሞተች በኋላ በቀብሯ ላይ የተገኙ ሰዎች በተህዋሲው መጠቃታቸው ነው የተነገረው።

ነርሷ ከሞተች ከ4 ቀናት በኋላ ነበር የተቀበረችው።

ምናልባት አስክሬን በማጠብ ላይ የነበሩ ሰዎች ተህዋሲውን እንዳዛመቱ ይገመታል።

ብዙውን ጊዜ በኢቦላ የሞቱ ሰዎች አስክሬን አደገኛና መርዛማ የኢቦላ ተህዋሲን የመሸከም አቅም አለው። የተህዋሲው እድሜም ከ2 ቀን እስከ 3 ሳምንት ይቆያል።

ኢቦላ ቺምፓዚን ከመሰሉ እንሰሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ ተህዋሲ ነው።

ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈውም በደም፣ በሰውነት ፈሳሽ ወይም ተህዋሲው ከነካው አካባቢ ሊሆን ይችላል። አሁን ሁሉም በተህዋሲው የተለከፉት እድሜያቸው ከ25 ዓመት በላይ የሆኑና የነርሷን ቀብር የታደሙት ናቸው።

የወረርሽኙን መቀስቀስ ተከትሎ ሴራሊዯንና ላይቤሪያ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ። የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ ለጤና ሚኒስትሮቻቸው ጉዳዩን በንቃት እንዲከታተሉ አዘዋል።

የቢቢሲ ዘጋቢ ከሴራሊዯን እንደጻፈችው በአገሪቱ ከኮቪድ ተህዋሲ በላይ ሕዝቡ ስጋት ያለበት ለኢቦላ ወረርሽኝ ነው።

ኢቦላ ተህዋሲ ድንገቴ ትኩሳት በመፍጠር በአጭር ሰዓት ታማሚውን በማዳከም የጡንቻ ከባድ ሕመም ፈጥሮ ጉሮሮን አቁሱሎ የሚገድል በሽታ ነው።

ከዚህም ባሻገር ማስመለስ፣ ማስቀመጥ እና የውስጥና የውጭ መድማትን ያስከትላል።

ታማሚዎች የሚሞቱት ብዙውን ጊዜ ፈሳሽ ከሰውነታቸው ተሟጦ ስለሚያልቅ ነው። ይህም የአንዳች ሰውነት አካል ሥራ ማቆምን ያስከትልና ለሞት ይዳርጋል።