የሳዑዲዋ የሴቶች መብት ተሟጋች ከእስር ተለቀቀች

የፎቶው ባለመብት, Lina Alhathloul
ታዋቂዋ የሳኡዲ አረቢያ የሴቶች መብት ተሟጋች ሉጃይን አል ሃትሎል ከእስር መፈታቷን ቤተሰቦቿ አስታውቀዋል።
የ31 ዓመቷ ሉጃይን አል ሃትሎል በሳኡዲ ሴቶች መኪና ማሽከርከር እንዲፈቀድላቸው ከፍተኛ አስተዋጽ አድርጋለች።
በአውሮፓውያኑ 2018 ላይ ክልከላው ከመነሳቱ ከሳምንታት በፊት ነበር በቁጥጥር ስር የዋለችው።
ታህሳስ ወር ላይ ደግሞ የአገሪቱ ፍርድ ቤት ፖለቲካዊ ስርአቱን ለመቀየርና የአገር መረጋጋትን በማወክ ጥፋተኛ ሆና አግኝቻታለሁ ብሎ ነበር። ይህን ውሳኔ ተከትሎም ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት ማረሚያ ቤት ውስጥ ስድስት ዓመት እንድታሳለፍ ተፈርዶባት የነበረ ቢሆንም ሁለት ዓመትና 10 ወራት ግን ተቀንሰውላታል።
ምንም እንኳን ሉጃይን አል ሃትሎል ከእስር ብትለቀቅም ሙሉ በሙሉ ነጻ አለመሆኗን ቤተሰቦቿ ገልጸዋል። አክለውም በርካታ ክልከላዎች እንዳሉባትና ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከአገር መውጣት እንደማትችል አስታውቀዋል።
''ሉጃይን ወደቤት ተመልሳለች'' ስትል እህቷ ሊና ረቡዕ ዕለት በትዊተር ገጿ ላይ በማስፈር የሴቶች መብት ተሟጋቿ ከ1001 ቀናት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ መለቀቋን አብስራለች።
ሌላኛዋ እህቷ ደግሞ ''በሕይወቴ ምርጥ የምለው ቀን ይህ ነው'' ስትል ደስታዋን ገልጻለች።
ሉጃይን 2018 ላይ እሷ እና በርካታ የሴቶች መብት ተሟጋቾች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ነበር በአገሪቱ የሴቶች መብት ተምሳሌት ተደርጋ መወሰድ የጀመረችው። በወቅቱ የሴቶች መብት ተሟጋቾቹ የአገሬው ሴቶች መኪና ማሽከርከር እንዲፈቀድላቸው መንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድረው ነበር።
ቤተሰቦቿ እንደሚሉት በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ለሶስት ወራት ምንም አይነት ግንኙነት ማድረግ አልቻሉም ነበር። በተጨማሪም በኤሌክትሪክ ሾክ ስቃይ ይደርስባት እንደነበር፣ ግርፊያ ይፈጸምባት እንደነበርና ጾታዊ ጥቃት እንደደረሰባት ገልጸዋል።
ምንም አይነት ስቃይ አልደረሰብኝም ብላ ቃሏን የምትሰጥ ከሆነ ደግሞ በነጻ እንደምትሰናበት ተነግሯት ነበርም ብለዋል ቤተሰቦቿ።
የሳዑዲ አረቢያ መንግስት የሚቀርቡበትን የማሰቃየት ክሶች ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጓል።
የመንግሥት ባለስልጣናት ሉጃን በቁጥጥር ስር የዋለችው ለሴቶች መብት ባደረገችው እንቅስቃሴ ሳይሆን ከውጭ አገር ዲፕሎማቶች፣ ከመገናኛ ብዙሀን እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በነበራት ግንኙነት ምክንያት ነው ብለዋል።
አሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ብሄራዊ የደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን የሉጃይን ከእስር መለቀቅ ዜና አስደሳች መሆኑን ገልጸው ''ጥሩ ነገር ነው'' በማለት ገልጸውታል።
ምንም እንኳን በሳዑዲ በርካታ የሴቶች መብት ተሟጋቾች በእስር ላይ የሚገኙ ቢሆንም የሉጃን ጉዳይ ግን ዓለማቀፍ ትኩረትን መሳብ ችሏል። ለማንም እጅ እንደማይሰጡ የሚነገርላቸው ቤተሰቦቿ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ተከታታይ የትፈታልን ዘመቻ ጉዳዩን ዓለም አቀፍ እንዲሆን አግዞታል።
የመታሰሯ ጉዳይ ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢል ሰልማንን ከሚያስተቹ ሁነቶች አንዱ ነው። ሴቶች መኪና እንዳይነዱ የሚከለክለውን ሕግ በማንሳትና ወግ አጥባቂዋን ሳኡዲ ለኢንቨስትመንት ክፍት በማድረግ ተራማጅ መሪ ቢባሉም፤ የመብት ተሟጋቾች መታሰር ግን በእጅጉ አስኮንኗቸዋል።












