ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንቶኒ ብሊንከን፡ አዲሱ ከፍተኛ የአሜሪካ ዲፕሎማት ማን ናቸው?
በአሜሪካ ጆ ባይደን አዲስ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ አዳዲስ ተሿሚዎችም የኃላፊነት ቦታቸውን ተቀብለዋል፤ ከነዚህም ውስጥ አንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ናቸው። አዲሱ ከፍተኛ የአሜሪካ ዲፕሎማት ማን ናቸው? የቢቢሲ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ልዩ ዘጋቢ ባርባራ ፕሌት አሸር በአንደበቷ ትነግረናለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ተሿሚዎችን ሹመት ስታደም ለሶስተኛ ጊዜዬ ነው።
አስታውሳለሁ የዶናልድ ትራምፕ ልዑካን ሬክስ ቲለርሰንና ማይክ ፖምፒዮ ሹመት ወቅት መረማመጃውም ሆነ አዳራሹ በሰው ተሞልቶ ነበር። በርካቶችም ደስታቸውን፣ ተስፋቸውን እንዲሁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቶች የተዥጎደጎዱበት ወቅት ነበር።
ለአዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሹመት ግን ሁሉ ፀጥ ረጭ ብሏል። ለዚህም ዋነኛው የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት በወጣው መመሪያ ምክንያት ነው።
ነገር ግን በርካቶች በዓለ ሲመታቸውን ባይታደሙም፤ ፊት ለፊት ተገኝተው እንኳን ደስ አለዎት ባይሉም በዲፕሎማቱ ማህበረሰብ ውስጥ የእፎይታ ስሜት ተፈጥሯል።
"ብዙዎች በብሊንከን መምጣት ከመጠን በላይ በፈንጠዝያ ላይ ናቸው፤ በሱ መምጣት ብቻ ሳይሆን የቀድሞው ቡድን ቢሮውን ለቆ በመውጣቱ" በማለት አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣን በቤታቸው በዓለ ሲመቱን እየተመለከቱ ባሉበት ነግረውኛል።
ብሊንከን አንጋፋ የሚባሉ ዲፕሎማት ናቸው። ለበርካታ አመታት በዘርፉ ላቅ ያለ ልምድን አካብተዋል። ነገር ግን በርካታ ሁኔታዎች ተቀይረዋል፤ "እምነትንና ሞራልና ለመመለስ የሚገጥማቸው ፈተና ቀላል ላይሆን ይችላል" ይላሉ እኚሁ ባለስልጣን።
በትራምፕ አስተዳደር ወቅት ሁኔታውን መቀበል ያቃታቸው 1 ሺህ ሰራተኞች ለቅቀዋል።
በሃሳብ ብንለያይም ከአስተዳደሩ ጋር እንቀጥላለን ያሉ ደግሞ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ዲፕሎማሲያዊ ያልሆነ አካሄድ ወደ ጎን በመገፋት፣ በሬክስ ቲለርሰን አጉል አሰራር በመሰላቸት እንዲሁ የትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊ በሆኑት ማይክ ፖምፒዮ ፖለቲካ ገሸሽ እንዲደረጉ ሆኗል።
"ሁላችንም ቢሆን በአለም ላይ ያለን ገፅታ መቀየሩ ከፍተኛ ደስታ ይሰጠናል" ይላሉ ባለስልጣኑ።
"በአራት አመቱ የትራምፕ አስተዳደር ገሽሽ ተደርጎ የነበረው ሁሉ ወደ ስራ ለመግባትና ነገሮችን ለመቀየር እየሞከረ ነው" በማለት ያክላሉ።
የፕሬስ ፅህፈት ቤቱ መተላለፊያ የነበረው የማይክ ፖምፒዮ ፎቶ ተነስቶ በምትኩ የተለያዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ፎቶ እንዲሰቀል ተደርጓል።
ከዚህም በተጨማሪ የሥራ አስፈላጊነትና ባለሙያነት ጋር የተያያዘ በማይክ ፖምፒዮ የተፃፈ ትልቅ ቢልቦርድ የጆ ባይደን በዓለ ሲመትን ተከትሎ እንዲወርድ ተደርጓል።
አዲሱ የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ላይ የረዥም አመት ልምድን አካብተዋል፤ ለዘመናትም የባይደን ቅርብ አማካሪ በመሆን ጠንከር ያለ ግንኙነትን መስርተዋል።
በሹመታቸው ወቅት ለዘብ ባለ ንግግግራቸው የትራምፕን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመቀልበስ እንደገና እንደሚፅፉት ያስገነዘቡ ሲሆን ከፍተኛ ድጋፍም ተችሯቸዋል።
የአሜሪካ እንደራሴዎችም ቢሆን ይህንን ከሌሎች አገሮች ጋር መጋተሩንና "አሜሪካ ትቅደም" የሚለውን አካሄድ ወደኋላ መተው ይፈልጋሉ።
ብሊንከን መጀመሪያ አከናውናቸዋለሁ ብለው ቃል የገቧቸው ጉዳዮች ቢኖሩ የሩሲያ ሳይበር ጥቃትና የምርጫ ጣልቃ መግባት ምላሽ፣ ሳዑዲ በየመን የምታደርገውን የአየር ጥቃት ማስቆም፣ በትራምፕ አስተዳደር አሸባሪ ተብለው የተፈረጁትን የሁቲ አማፅያን ሁኔታ እንደገና መገምገም የሚሉ ናቸው። የሁቲ አማፅያን በአሸባሪነት መፈረጅ በየመን ያለውን የሰብዓዊ እርዳታዎች ላይ እክል ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ይታመናል።
ኢራንን በተመለከተ ብሊንከን ባይደን ቃል የገቡትን የደገሙ ሲሆን ይኸም የ2015ቱን የኢራን የኒውክሊየር ስምምነትን መመለስ ነው።
ባራክ ኦባማ በስልጣን ዘመናቸው ወቅት አሳክተዋቸዋል ከሚባሉት ጉዳዮች ውስጥ (JCPOA) ተብሎ የሚጠራው የኢራን የኒውክሊየር ፕሮግራም ሲሆን ፕሬዚዳንት ትራምፕ በ2018 ስምምነቱን አፍርሰዋል።
ወደ ስምምነቱ እንዲመለሱ ግን ኢራን የገባችውን ቃል ስታከብር እንደሆነና ይህ የማይሆን ከሆነ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል ይላሉ።
ቻይናን በተመለከተ ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጠንከር ያለ አስተያየትና አካሄድ ጋር ይስማማሉ። ቻይናን ለማዳከም ትራምፕ ውድቅ ካደረጓቸው የዲሞክራሲ ደጋፊዎችና አለም አቀፍ ተቋማት ጋር መተባበር ያስፈልጋል በማለት አፅንኦት ይሰጣሉ።
የአዲሱ ከፍተኛ ዲፕሎማት ዋነኛ አላማና ተልዕኮ የአሜሪካን መሪነት ቦታ እንደገና በዚያ መንገድ መመለስ ነው።
ነገር ግን በተሾሙበት ቀን ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ውይይት በመጥፎ ይታይ ከነበረው የአሜሪካ አስተዳደር ጋር ተያይዞ እንዴት የቀድሞ አጋሮቿ ያምኗታል የሚል ነበር ።
ነገር ግን ብሊንከን አሜሪካ ወደቀደመ ስፍራዋ ለመመለስ ያለው ፍላጎት ከአጋሮቿም በኩል የመጣ ነው ይላሉ።
በመጀመሪያ ቀናቸው ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ውይይት ከሚዲያውና ከጋዜጠኞች ጋር ለመስራት ያላቸውን ቀናነት በግልፅ አሳይተዋል። ይህ አካሄድ ደግሞ ከቀድሞው አስተዳደደር ተቃራኒ ነው።
ማይክ ፖምፒዮ እንደ አለቃቸው ሚዲያን አይወዱም አያዳምጡም፤ አንዳንድ ጊዜም ሲያወግዙ ይሰማሉ።
ለጥያቄዎቻችን ኢሜይል መልስ ለማግኘት በጣም ፈታኝ ነበር። ደፈር ያሉ የኮሚዪኒኬሽን ቡድኑ አባላት ምንም የምንለው የለም የሚል መልስ ይሰጡን ነበር።
የብሊንከን አካሄድ ልታይ ልታይ ይሉ ከነበሩት የማይክ ፖምፒዮ ሁኔታ ተቃራኒ ነው።
ሆኖም በአሁኑ ወቅት በአዲሱ አስተዳደር የፕሬዚዳንቱ የአየር ንብረት ለውጥ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑትና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው ከፍተኛ ስፍራ የተጎናፀፉት የቀድሞ አለቃቸው ጆን ኬሪ ጋር ይወዳደራሉ።
ነገር ግን ብሊንከንም ቢሆኑ ለየት ያለ ባለታሪካቸው የተጎናፀፉት ማንነት አለ።
አያታቸው በሩሲያ የነበረውን የፀረ- ይሁዲዎች ነውጥ ፈርተው ወደ አሜሪካ በስደት መጡ፤ ፖላንዳዊ እንጀራ አባታቸው እንዲሁ በናዚዎች ከተቃጣባቸው ግድያ በአሜሪካውያን ወታደሮች የዳኑ ናቸው።
"ማንነታችን ይኼ ነው። በአለም ላይ የምንወክለውም ይህንኑ ነው። እንደ ሰው ጉድለቶች ቢኖሩንብንም ምርጥ ለመሆን እንሞክራለን" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት አሜሪካ አሁንም ቢሆን ጠቃሚነቷን ማረጋገጥ የስራቸው ማዕከል እንደሆነ ያስባሉ።