ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“ትራምፕ የደህንነት መዋቅሩን አላሽቀዋል" ፡ ባይደን
ተሰናባቹ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአሜሪካ ደህንነት ቁልፍ የሆኑ የጸጥታ ተቋሞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱ ጆ ባይደን ተናገሩ።
ተመራጩ ፕሬዘዳንት ባይደን፤ የትራምፕ አስተዳደር የደህንት መዋቅሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳስከተለ ገልጸዋል።
የሥልጣን ሽግግር እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት የባይደን ቡድን ከመከላከያና ከሌሎችም ተቋሞች አስፈላጊውን መረጃ አለማግኘቱንም አክለዋል።
ባይደን ጥር 20 በይፋ ሥልጣን የሚረከቡ ቢሆንም፤ ትራምፕ የምርጫውን ውጤት ስላልተቀበሉ ባይደን ከደህንት ቢሮው ጋር እንዳይገናኙ አሰናክለዋል።
ባይደን ስለ ትራምፕ ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ፤ የአገሪቱ ተጠባባቂ የመከላከያ ጸሐፊ ክሪስቶፈር ሚለር “ሽግግሩን ለመደገፍ የተቻለንን እየጣርን ነው” ብለዋል።
ከ400 በላይ ባለሥልጣኖች ጋር 164 ቃለ መጠየቅ ተደርጎ ከ 5,000 ገጽ በላይ መረጃ እንደተገኘ ገልጸዋል። ይህም ባይደን ከጠየቁት በላይ እንደሆነ አክለዋል። የፔንታጎን ቃል አቀባይም ድርጅቱ ለባይደን “ግልጽ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ባይደን እንደሚሉት፤ ቡድናቸው ከመከላከያው አስተዳደራዊ እና ከበጀት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች መረጃ ማግኘት አልቻለም።
“ተሰናባቹ አስተዳደር በደህንነት ጉዳዮች ላይ የምንፈልገውን መረጃ እየሰጠን አይደለም። ይህ ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ነው” ብለዋል።
አስተዳደራቸው አሜሪካ በመላው ዓለም ስላላት ስምሪት መረጃ እንደሚፈልግም ባይደን አክለዋል።
“ለደህንነታችን ቁልፍ የሆኑ ተቋሞች በከፍተኛ ሁኔታ ላሽቀዋል። በግል ጉዳይ፣ በአቅም ማነስ እና ሞራል በማጣት ይፈተናሉ። የፖሊሲ ጉዳይ ችላ ተብሏል” በማለት ንግግር አድርገዋል።
ትራምፕ ከምርጫው በኋላ የደህንት አመራር የነበሩት ማርክ ኤስፔርን ከሥልጣናቸው አንስተዋል። ትራምፕ የጸረ ዘረኝነት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ መከላከያ ለማሰማራት ማቀዳቸውን በመቃወማቸው ነው አመራሩ ከኃላፊነት የተወገዱት።
ትራምፕ በደህንነት ቢሮው ለሳቸው ታማኝ የሆኑ ሰዎችን መቅጠራቸውን የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው ሲተቹ ነበር።
የትራምፕ እርምጃ አመራራቸው ከሥልጣን ከመውረዱ በፊት ቀውስ ለመፍጠር የተቃጣ እንደሆነም ሰግተዋል።