ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፓኪስታን፡ አሜሪካዊውን ጋዜጠኛ ቀልተው ገድለዋል የተባሉት ግለሰቦች በነፃ ተሰናበቱ
አሜሪካዊውን የዋል ስትሪት ጋዜጠኛ ዳንኤል ፐርልን ገድለዋል የተባሉት አራት ግለሰቦችን የፓኪስታን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከወንጀሉ ነፃ ናችሁ ብሎ አሰናብቷቸዋል።
ዳንኤል ፐርል የተገደለው በአውሮፓውያኑ 2002 ነው።
በደቡብ እስያ የነበረው የዋል ስትሪት ጆርናል ኃላፊ የነበረው ዳንኤል በፓኪስታን ፅንፈኛ ቡድኖች ላይ አንድ ሪፖርት እያዘጋጀ በነበረበት ወቅት ነው ታግቶ፣ ከዚያንም አንገቱ ተቀልቶ የተገደለው።
ግድያውን በዋነኝነት በማቀናበር ተከሶ የነበረው ትውልደ እንግሊዛዊ ታጣቂ ሲሆን በዚህ ጠለፋና ግድያ ሌሎች ሶስት ተባባሪዎች እንዲሁ ተከሰው ነበር።
ነገር ግን የፓኪስታን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግለሰቦቹን በነፃ አሰናብቷቸዋል።
የጋዜጠኛው ቤተሰቦች ጠበቃ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳስደነገጣቸውና "ለፍትህ አሳዛኝ ቀን" ሲሉ ጠርተውታል።
ነገር ግን የአሜሪካ ባለስልጣናት እጃችን አጣጥፈው እንደማይቀመጡ ያስታወቁ ሲሆን የግድያው አቀነባባሪ ነው የተባለው ኦማር ሼክን በአሜሪካ ክስ እንደሚከፍቱበት አስጠንቅቀዋል።
ዳንኤል ፐርል እንዴት ተገደለ?
በአውሮፓውያኑ 2001 መስከረም ላይ በአሜሪካ በደረሰው ሽብር ጥቃት ማግስት የዋል ስትሪቱ ጆርናል ጋዜጠኛ ዳንኤል ፐርል ፅንፈኛ ታጣቂ ቡድኖችን በተመለከተ አንድ ሪፖርት ለማጠናቀር ወደ ፓኪስታን አቀና። ነገር ግን ያልተጠበቀው ሆኖ ራሱ ሰለባ ሆነ።
በመጀመሪያ በሰንሰለት ታስሮና ሽጉጥ ተደግኖበት ፎቶዎች ወጥቶ የነበረ ሲሆን በኋላም ተቀልቶ ተገደለ። አሰቃቂ ግድያው በቪዲዮ የተቀረፀ ሲሆን አልቃይዳና አይኤስ በሚያደርጓቸው የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮዎች ተመሳሳይ ቪዲዮ እንዲጠቀሙ ምክንያት የሆነው ይኸው የዳንኤል ፎቶ ነው።
በግድያው ተከሶ የነበረው ኦማር ሼክ የተወለደው በእንግሊዝ ሲሆን በለንደን በሚገኘው የስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ትምህርቱን ተከታትሏል።
በጎሮጎሳውያኑ 1995 ምዕራባውያን ቱሪስቶችን በማገት በህንድ ለእስር ተዳርጎ ነበር።
እሱም ሆነ ሁለት ታጣቂዎች ከአምስት አመት በኋላ በነፃ ተለቀዋል።በነፃ የተለቀቁበት ምክንያት ታጣቂዎች ታሊባን በሚቆጣጠሩት አፍጋኒስታን አውሮፕላን ጠልፈው መንገደኞቹን ነፃ ለማውጣት እነ ኦማር እንዲፈቱና በልውውጥ እንዲሆን መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው።
ኦማርና ዳንኤል የተገናኙት በፓኪስታኗ ከተማ ራዋንፒንዲ በጎሮጎሳውያኑ 2002 ነው። ኦማር ሃሰተኛ ስም ሰጥቷታል የተባለ ሲሆን ዳንኤል ለሪፖርቱ ማናገር የሚፈልገው ፅንፈኛ የሚባል ታጣቂ ተከታይ እንደሆነ ኦማር ነገረው።
ኦማር ከሰውየው ጋር አገናኝሃለሁ እንዳለውና ነገር ግን ጋዜጠኛውን ወጥመድ ውስጥ እንዳስገባው ተነግሯል።
ዳንኤል ካራቺ ወደምትባለው የወደብ ከተማ ባቀናበት ወቅት ታገተ። የአጋቾቹ ጥያቄ የነበረው በአሜሪካ ኃይሎች በጓንታናሞ ቤይ እስር ላይ ላሉ የተሻለ አያያዝ እንዲኖር፣ በጓንታናሞ የታሰሩ ፓኪስታናውያን እንዲለቀቁ የሚል ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ ለፓኪስታን ቃል ገብታው የነበረውን ተዋጊ ጄቶች አንድትሰጣት ወይም ገንዘቧን እንድትመልስ የሚለውም ሌላኛው ጥያቄያቸው ነበር። በመጨረሻ ዳንኤል ፐርል የሞሳድ ሰላይ ነህ በሚል ተገድሏል።
ለምን በነፃ ተሰናበቱ?
ምርመራ ከተካሄደ በኋላ ነበር ኦማርና ሶስት ተባባሪ የተባሉት የታሰሩት፤ ክስም ተመሰረተባቸው።
ኦማር ሼክ እገታውን ስለማቀናበሩና በራዋልፒንዲ በሚገኝ ሆቴል ጋዜጠኛውን ማግኘቱን ሁለት የአይን እማኞች መስክረዋል። ነገር አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ ከፍተኛ ችግር የተስተዋለበት ነው ተብሏል።
ምንም እንኳን ብዙዎች ኦማር ለፓኪስታን የደህንነት ሰራተኞች ራሱን አሳልፎ ነው የሰጠው ቢሉም ፖሊስና አቃቤ ህግ በበኩላቸው በካራቺ አየር ማረፊያ ከሳምንት በኋላ በቁጥጥር ስር ነው የዋለው ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ኦማር ሼክ ራሱ ግድያውን እንዳልፈፀመ መረጃዎች መውጣት ጀመሩ።
በአሁኑ ወቅት የሚታሰበው የአልቃይዳ ከፍተኛ ኃላፊና በአሁኑ ወቅት በጓንታናሞ ቤይ ያለ ካሊድ ሼክ መሃመድ የተባለ ግለሰብ ለግድያው ጥፋተኛ እንደሆነ ነው።
ነገር ግን የፓኪስታን ባለስልጣናት ሆን ብለው የምስክሮችን እማኝነት ውድቅ አድርገውታል ተብሏል።
ስማችን አይጠቀስ ያሉ በምርመራው ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው ሁለት ግለሰቦች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ክሱ የተያዘበት መንገድ አሳዛኝ ነው ብለዋል።
በግድያው ወቅት የተፈጠሩ ሁኔታዎችን አለማጤን እንዲሁም ግድያው ተፈፀመ በተባለበት ወቅት ኦማር በቦታው አለመገኘቱ ክሱን ውሃ እንዳይቋጥር አድርጎታል ይላሉ።
ነገር ግን መርማሪዎቹ ኦማር ግድያውን አቀናብሯል ብለው ያምናሉ።
በባለፈው አመት በሲንድ የሚገኝ የፓኪስታን ፍርድ ቤት ኦማርና ሶስቱ ተባባሪ የተባሉትን ግለሰቦች በነፃ አሰናብቶ ነበር።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በተለያዩ ሚዲያዎች ከፍተኛ ውግዘት በማስከተሉ የዳንኤል ቤተሰቦችና አቃቤ ህግ ውሳኔው እንዲቀለበስ ይግባኝ እስኪጠይቁ ግለሰቦቹ በእስር ላይ እንዲቆዩ ተደርገው ነበር።
ነገር ግን የፓኪስታን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኙን ውድቅ አድርጎ ውሳኔው እንዲፀና አድርጓል።