ከዓመታት ዕገዳ በኋላ በሞስኮ ሴት ሾፌሮች ባቡር እንዲዘውሩ ተፈቀደላቸው

ሥራ የጀመሩት 12 የባቡር አሽከርካሪዎች

የፎቶው ባለመብት, MOSCOW METRO

የምስሉ መግለጫ, ሥራ የጀመሩት 12 የባቡር አሽከርካሪዎች

በሩሲያዋ መዲና ሞስኮ ሴት ሾፌሮች የከተማዋን ባቡር እንዳያሽከረክሩ ለዘመናት ተጥሎ የነበረው ክልከላ ተነስቶ ወደሥራ እንዲመለሱ ተፈቀደ።

የከተማዋ የትራንስፖርት ባለሥልጣን ሴቶች የኤሌክትሪክ ቀላል ባቡር እንዲሾፍሩ መፈቀዱ አዲስ ዘመን እየመጣ መሆኑን አመላካች ነው ሲል አሞካሽቶታል።

12 የሚሆኑ ሴቶች በሞስኮ ባቡር እንዲያሽከረክሩ ሰልጥነው ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል። ከፈረጅኖቹ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ወር ጀምሮ ባቡር መዘወር መብታቸው ነው ተብሏል።

የሞስኮ ቀላል ባቡር ሴቶችን ባቡር እንዳይዘውሩ በሚል ሴት መቅጠር ያቆመው ከዛሬ 40 ዓመት በፊት ነው። የመጨረሻዋ ሴት የባቡር አሽከርካሪ ሥራውን የለቀቀችው ደግሞ በፈረንጆቹ 2014 ነበር።

ባቡር መዘወር በሞስኮ ሴቶች እንዳይሰሯቸው ከተደረጉ ዝርዝር የሥራ ዘርፎች አንዱ ሆነ ተመዝግቦ ነበር። ሆኖም ከዚህ ዝርዝር እንዲወጣ የተደረገው በቅርብ ነው።

ሴቶች እንዳይሰሯቸው ከሚባሉ የሥራ ዘርፎች ውስጥ ተሳቢ መኪና መንዳትና ጀልባ መቅዘፍም እንደ ባቡር መዘወር ሁሉ ከክልከላው የወጡት ቴክኖሎጂ እነዚህን ሥራ ለመሥራት የጉልበት ጥንካሬን ስለማይፈልግ ነው ተብሏል።

አሁን የተመረቁት 12 የባቡር ዘዋሪዎች ሥራ ሲጀምሩ ከፈለጉ ሱሪ ካሻቸው ደግሞ አጭር ቀሚስ መልበስ ተፈቅዶላቸዋል። የተመቻቸውን መልበስ መብታቸው ነው ተብሏል።

በሩሲያ 356 ዓይነት ሥራዎች ላይ ሴቶች እንዳይሰማሩ የሚያዝ ደንብ ለዓመታት ተቀምጦ እስከዛሬም አለ። ይህ ደንብ ሴቶች በሰዓት ለሁለት ጊዜ ያህል ማንኛውም ሥራ ቢሆን 10 ኪሎ ግራምና ከዚያ በላይ ማንሳት የሚያስገደድ ከሆነ ከባድ የጉልበት ሥራ ስለሆነ ወንዶች ብቻ ይስሩት ይላል።

የሩሲያ የሴቶች መብት ተቆርቋሪዎች ይህን ደንብ ሲሳለቁበት ኖረዋል። "የአንድ ዓመት ሕጻን አማካይ ክብደት 10 ኪሎ ነው። ስለዚህ በደንቡ መሠረት ልጆቻችንን ማቀፍ ልንከለከል ይገባል" ሲሉ።

በቅርብ ጊዜ የሴቶች መብት ተቆርቋሪዎች ይህ ያረጀና ያፈጀ ጾተኛ ደንብ እንዲሰረዝ ፍርድ ቤት ድረስ አቤቱታ አቅርበዋል። በዚህም ተጋድሎ ለሴቶች የተከለከሉ የሥራ ዘርፎች ዝርዝር ከ365 ወደ 96 ወርዷል።

አሁን ክልክል የተደረጉት የሥራ ዘርፎች በብዛት ከኬሚካልና ከፈንጂ ጋር የተያያዙት ብቻ ናቸው።

የሚገርመው በሩሲያ ሴቶች ከ1936 (እአአ) ጀምሮ ባቡር የመዘወር መብት ነበራቸው። ይህ መብት የተገፈፈው ከ1980 በኋላ ነው።

የሞስኮ ሜትሮ [የምድር ውስጥ ባቡር] በሚቀጥለው ዓመት ተጨማሪ ሴቶችን በሾፌርነት ለመቅጠር አስቤያለሁ ብሏል።