ሙዚቃ ፡ በ2021 የሙዚቃ ድግሶች ወደ መድረክ ይመለሱ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፈረንጆቹ 2020 ምን መልካም ነገር ትቶ አለፈ ቢባል ሙዚቃ ማለት ይቻላል።
እንግሊዛዊቷ ዱዋ ሊፓ እና ሌዲ ጋጋ ከቤታቸው ሆነው በበይነ መረብ አድናቂዎቻቸውን አስጨፍረዋል። በርካታ ተወዳጅ ሙዚቀኞች አልበሞቻቸውን ለአድናቂዎቻቸው አቅርበዋል።
እርግጥ ነው ሰዎች በአካል ሄደው የሚታደሙበት የሙዚቃ ድግስ አልነበረም - ለኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት።
ነገር ግን ይህ ለአርቲስቶች መነቃቃት ሆናቸው እንጂ ሥራ የለም ብለው እንዲቀመጡ አላደረጋቸውም።
ቻርሊ ኤክስሲኤክስ የተሰኘችው ወጣት ዘፋኝ በስድስት ሳምንታት አገባዳ የለቀቀችው አልበም በሚሊዮኖች ተቸብችቦላታል።
አንጋፋው ፖል ማካርቲኒ ከ50 ዓመት በፊት የጀመረውን አልበም ዘንድሮ አጠናቋል። ቴይለር ስዊፍት ደግሞ በአምስት ወራት ውስጥ ሁለት አልበም ለአድናቂዎቿ አበርክታለች።
አሁን ጥያቄው እውን በሚቀጥለው በዚህ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት 2021 የሙዚቃ ድግስ [ኮንሰርት] ይመለስ ይሆን ወይ? የሚለው ነው።
የኢንተርኔት ድግሶች
2021 የኢንተርኔት [በይነ መረብ] ድግሶች የሚደምቁበት እንደሚሆን ይገመታል።
ኮሮናቫይረስ የአርቲስቶች ጓዳ ጎድጓዳ አድናቂዎቻቸው እንዲያዩ አድርጓል። አብዛኞቹ ሙዚቀኞች ድግሳቸውን ሲያቀርቡ የነበሩት ከመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ነው።
እንደው የታዋቂ ሰዎች ኩሽና እንደኛው ይሆን? ብለው ይጠይቁ ለነበሩ 2020ን ያክል ለጋስ ዓመት የለም።
የምርም ፈረስ የሚያስጋልብ መኖሪያ ቤት ያላቸው ዘፋኞች ከኩሽና እስከ መኝታና መታጠቢያ ቤታቸው እየተሽከረከሩ በእጃቸው በያዙት ድምፅ ማጉያ ሲቀኙ ነበር።
ዱዋ ሊፓ የተሰኘችው አዲስ ሙዚቀኛ ባለፈው ኅዳር ከጓዳዋ ሆና ያስተላፈችው ድግስ በኢንተርኔት ዓለም ብዙ ሰዎች ያዩት ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, LIVENOW
ሙዚቀኛዋ ከቤት ያስተላለፈችው ድግስ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ወጥቶበታል። ድግሱን በኢንተርኔት ለመከታተል በቻይናና ሕንድ ብቻ 284 ሺህ ሰዎች ቲኬት ገዝተዋል።
ሙዚቀኛዋ እንዲህ በጉጉት የተጠበቀውን ድግስ እንደዋዛ አላየችውም። ከኋላዋ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዳንሰኞች አሰልፋ ነበር። እንደ ኤልተን ጆን ያሉ ሙዚቀኞች ተጋባዥ ሆነው መጥተው አድምቀውታል።
አሜሪካዊ ራፐር ትራቪስ ስኮት ደግሞ በሌላ ዓይነት ነው ብቅ ያለው።
ራፐሩ 'ፎርትናይት' በተሰኘው የቪድዮ ጌም ነው የዘጠኝ ደቂቃ ሙዚቃውን ያስኮመኮመው። ለዚህም 20 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሎታል።
ትራቪስ በ2018/19 ለ58 ቀናት ተዘዋውሮ ከሠራው የሙዚቃ ድግስ ያገኘው ገንዘብ 53 ሚሊዮን ዶላር ነበር።
የበይነ መረብ ሙዚቃ ድግስ ሌላኛው ጥቅም ተመልካቹ በፒጃማው ሆኖ ከቤቱ መከታተል መቻሉ ነው። የሚወዱትን ሙዚቀኛ ለማየት ወደ ትልቅ ከተማ መሄድ አይጠበቅብም ማለት ነው።
ከዚህም አልፎ የኢንተርኔት ኮንሰርት ቦታ ሞልቷል አይል፤ ዕድሜዎ አልደረሰ አይል። [ለምሳሌ የዱዋ ኮንሰርት ዋጋው 7.50 ዩሮ ነበር።]
ኮሮናቫይረስ በክትባት ተሸንፎ ቢጠፋ እንኳ ኮንሰርቶች ቶሎ ወደ መድረክ ይመለሳሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።
ድግሶች ይመለሳሉ - ግን እንዴት?
አንዳንዶች የሙዚቃ ድግስ በሚቀጥለው ፋሲካ ይመለሳል ይላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ክረምት ላይ ሳይመለስ አይቀርም ባይ ናቸው።
አንዳንድ ሙዚቀኞች ለሚቀጥለው ዓመት ከአሁኑ የድግሳቸውን መግቢያ በመሸጥ ላይ ናቸው። ሌሎች ደግሞ መጪው ዘመን አያስተማምንም በማለት እየሰረዙ ይገኛሉ።
ኮሮናቫይረስ ቢቀንስ እንኳ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ግዴታ ይሆናል።
ወደ ድግስ ሲሄዱ የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረግ ደግሞ ሌላኛው የመጪው ዘመን እውነታ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ይህን ሁሉ ከምናደርግ ለምን ታዳሚዎችን በፀረ-ተህዋስ ፈሳሽ አንረጫቸውም ያሉም አልጠፉም። አካላዊ ርቀት ሳይጠበቅ ሲቀር በጩኸት የሚያሳብቅ የእጅ አምባር ይገጠም የሚል ሐሳብም ተሰምቷል።
'ቲኬትማስተር' የተሰኘው የሙዚቃ ድግሶች አዘጋጅ ተቋም ሰዎች ኮቪድ-19 እንደሌለባቸው የሚያረጋግጥ ሠርቲፊኬት ከሌላቸው ቲኬት እንዳይገዙ መከልከል አለባቸው ይላል።
ያም ሆነ ይህ ወደፊት የሙዚቃ ድግሶች ልክ እንደቀድሞው እየተፋፈጉ የሚታደሟቸው ይሆናሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስላል።
እና በአዲሱ ዓመት ከምዕራባዊያኑ ሙዚቀኞች ምን ይጠበቃል?
ታዋቂዋ አሜሪካዊት ሶፍት ሮክና ካንትሪ ሙዚቀኛ ቴይለር ስዊፍት በተጠናቀቀው 2020 ባወጣችው አልበም ለግራሚ ሽልማት ታጭታለች።
ሙዚቀኛዋ ከዚህ በፊት የሠራቻቸውን ሥራዎች ስቱዲዮ ገብታ ድጋሚ መቅረፅ ትፈልጋለች።
ለምን ካሉ ነገሩ ወዲህ ነው። የሙዚቀኛዋ የቀድሞ ሥራዎች ባለቤት እሷ አይደለችም፤ የቀድሞ ድርጅቷ እንጂ።
የቴይለር ሙዚቃዎች መብት ያለው ድርጅት የዘፋኟን ሥራዎች በ300 ሚሊዮን ዶላር እንደሸጠ ተዘግቦ ነበር።
አሁን ድጋሚ መቅዳት ያሻትም የኮፒ ራይት መብቷን ድጋሚ ለመቆጣጠር ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አዴልና ሪሃና አልበም አይለቁም?
ተወዳጆቹ አዴልና ሪሃን ከዛሬ ነገ አልበም ይለቃሉ ተብሎ ቢጠበቅም በአድናቂዎቻቸው ላይ ጨክነዋል።
በሚቀጥለው ዓመት ጠብቁን እያሉን ይሄው አዲስ የሙዚቃ ሥራ ካስደመጡ ሦስት ዓመት ሆናቸው።
ሪሃና በሰባት ዓመት ሰባት አልበሞችን አከታትላ አድናቂዎቿን በተወዳጅ ሙዚቃዎቿ ፍቅር ካጨናነቀች በኋላ ትኩረቷን ወደ ፋሽን አዙራለች።
በአድናቂዎቿ ዘንድ ሪሪ በተሰኘ ቅፅል ስሟ የምትቆላመጠው ሪሃና ለኮቪድ-19 እንዲሆን ብላ ሚሊዮን ዶላሮች ለግሳለች።
አዴልም እንዲሁ የሙዚቃ አልበም የማውጣቷ ነገር አጠራጣሪ ነው።
ነገር ግን ድሬክ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ሙዚቃ ይለቃል ተብሎ ይጠበቃል።
















