ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ምርጫ፡ ጆ ባይደን በመራጭ ወኪሎች የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው በይፋ ተሰየሙ
ጆ ባይደን የምርጫ ድላቸው በመራጭ ወኪሎች ስብስብ (ኤሌክቶራል ኮሌጅ) ተረጋግጦላቸው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው በይፋ ተሰይመዋል፡፡
ይህንን የድምጽ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ተከትሎ ባይደን ባደረጉት ንግግር "በመጨረሻም የሕዝቡ ፍላጎት አሸነፈ" ብለዋል።
በአሜሪካ የምርጫ አሰራር መሰረት ሕዝብ ድምጽ የሚሰጠው በቀጥታ ለእጩ ፕሬዝዳንቶች ሳይሆን የግዛት ወኪሎችን ለመምረጥ ነው፡፡ በዚህ መንገድ 270 እና ከዚያ በላይ ድምጽ ውክልና ያገኘ አሸናፊ ይሆናል፡፡
በመጨረሻ እነዚህ የድምጽ ሰጪ የግዛት ወኪሎች ተሰባስበው በሕዝብ የተቀበሉትን ውክልና በድምጻቸው በማረጋገጥ ፕሬዝዳንቱን በይፋ ይመርጣሉ፡፡
ባይደን በአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸው በዚህ መንገድ በይፋዊ መረጋገጡን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር፤ የአሜሪካ ዴሞክራሲ "ተገፍቶ፣ ተፈትኖ እና ስጋት ላይ ወድቆ ነበር" ካሉ በኋላ፤ የአሜሪካ ዴሞክራሲ፤ "እውነተኛ እና ጠንካራ መሆኑን አፈር ልሶ በመነሳት አረጋግጧል" ብለዋል።
ባይደን ፕሬዝደንት ትራምፕ የምርጫውን ውጤት ለማስቀየር ያደረጉትን ጥረት ፍሬ ባለማፍራቱ አሁን ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ የምንሸጋገርበት ጊዜ ነው ብለዋል።
ይህ በኤሌክቶራል ኮሌጁ የሚሰጠው ማረጋገጫ ባይደን ወደ ዋይት ሃውስ እንዲገቡ ማግኘት የሚገባቸው የመጨረሻው ማረጋገጫ የድምጽ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ነው።
በአሜሪካ ምርጫ ስርዓት ውስጥ መራጮች ድምጻቸውን ለኤክቶራል ኮሌጅ መራጮች በየግዛቶቻቸው ከሰጡ በኋላ አሸናፊዎቹ "ኤሌክተርስ" በዚህ መንገድ ተሰባስበው ለፕሬዝደንታዊ እጩዎች ድምጻቸውን ይሰጣሉ።
በአሜሪካ የምርጫ ውጤት መሠረት ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ከወር በፊት በተካሄደው ምርጫ 306 ኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጽ ሲያገኙ ፕሬዝደንት ትራምፕ ደግሞ 232 ላይ መቆማቸው ይታወሳል፡፡
እስካሁን የምርጫውን ውጤት አልቀበልም የሚሉት ፕሬዝደንት ትራምፕ፤ ባይደን ምርጫውን ማሸነፋቸው በአሌክቶራል ኮሌጅ ከተረጋገጠ በኋላ ያሉት ነገር የለም።
ትራምፕ ምርጫው ተጭበርብሯል ሱሉ ቢቆዩም ለዚህ ክሳቸው ግን እስካሁንም ማረጋገጫ ማቅረብ አልቻሉም። ስለመጭበርበሩ ለማስረዳት ጉዳያቸውን ወደ ተለያዩ ፍርድ ቤቶች ይዘው ቢሄዱም ክሳቸው ውድቅ ተደርጎባቸዋል።
ምንም እንኳ ትራምፕ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም በሚል አቋማቸው ቢጸኑም አንዳንድ የሪፓብሊካን ሴናተሮች ግን ትራምፕ የምርጫውን ውጤት በጸጋ እንዲቀበሉ ጥሪ እያቀረቡላቸው ይገኛሉ።
የምርጫው ውጤት መረጋገጡን ተከትሎ ሪፓብሊካኑ ሴናተር ላማር አሌክሳንደር፤ "ፕሬዝደንታዊ ምርጫው ተጠናቋል። ግዛቶችን የምርጫውን ውጤት አረጋግጠዋል። ፍርድ ቤቶች ለክርክሮች ብይን ሰጥተዋል። የመራጭ ወኪሎች ‹ኤሌክተርስ› ድምጽ ሰጥተዋል። ፕሬዝደንት ትራምፕ ለአገራቸው ቅድሚያ ሰጥተው፤ለተመራጩ ፕሬዝደንት ባይደን መልካም ጅማሮ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተስፋ አድርጋለሁ" ብለዋል።
"ኤልክቶረስ" በተለያዩ ግዛቶች ድምጻቸውን በሰጡበት ወቅት ከፍተኛ የደህንነት ጥበቃ ተደርጓል።
በተለይ በሚሺጋን ግዛት የደህንነት ስጋት ሊኖር እንደሚችል ጥቆማ በመሰጠቱ አንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ እንዲሆኑ ተደርገው ነበር።