ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትግራይ ፡ በሳምንቱ ማብቂያ መቀለ ያስተናገደቻቸው አበይት ክንውኖች
ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የፌደሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል አስተዳደር እንዲፈርስ ከወሰነ በኋላ የተሰየመው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሥራው እንደሚጀምር ተነግሯል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) ጠቅሶ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው፣ በክልሉ በነበረው ግጭት ምክንያት ከአንድ ወር በላይ ሥራ አቁመው የሚገኙ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ቅድመ ዝግጅቶች ተደርጓል።
በዚህም ለሳምንታት ሥራ ያቆሙ የመንግሥት ሠራተኞች ከዛሬ ሰኞ ታህሳስ 05/2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን የማይመለሱ ሠራተኞች ግን በገዛ ፍቃዳቸው ሥራቸውን እንደለቀቁ ተደርጎ እንደሚቆጠር ጊዜያዊ አስተዳደሩ ገልጿል።
በክልሉ የሚገኙ የንግድ ድርጅቶችም ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለስ አለባቸው ያሉት ሙሉ ነጋ (ዶ/ር)፤ ይህን በማያደርጉ የንግድ ድርጅቶች ላይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እርምጃ መውሰድ ይጀምራል ብለዋል።
ጦር መሳሪያ ማስረከብ
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ውስጥ መደበኛ እንቅስቃሴዎችን ከማስጀመር በተጨማሪ "በሕጋዊም ሆነ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የጦር መሳሪያ ታጥቆ የሚገኝ ማንኛውም ግለሰብ እስከ ማክሰኞ ታህሳስ 6 ድረስ ትጥቁን በአቅራቢያው ለሚገኝ የጸጥታ አካል እንዲያስረክብ" መታዘዙን ዶክተር ሙሉን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
ከዚህ በተጨማሪም የጦር መሳሪያዎችን በፈቃደኝነት የማስረከቢያ ጊዜው ሲጠናቀቅ የጸጥታ አካላት ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ለመያዝ የቤት ለቤት ፍተሻ እንደሚያደረጉ ተገልጿል።
በዚህም ጊዜ የጦር መሳሪያዎች የሚገኙባቸው ግለሰቦች በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ የጊዜያዊ አስተዳዳሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ሞባይል እና ኤሌክትሪክ በመቀለ
የወታደራዊ ግጭቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል የኤልክትሪክ፣ የስልክና የኢንተርኔት አግልግሎት ለሳምንታት ተቋርጦ ቆይቷል። ከሳምንት በፊት በአንዳንድ አካባቢዎች አገልግሎቶቹ መልሰው ቢጀምሩም በክልሉ ዋና ከተማ ግን አስከ ቅዳሜ ድረስ ተቋርጦ ቆይቷል።
በዚህም በርካቶች በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው የሞባይል ድምጽ አገልግሎት በመቀለ እና በማይጨው ከተሞች መጀመሩን ኢትዮቴሌኮም ያስታወቀው ቅዳሜ ታህሳስ 3/2013 ዓ.ም ነበር።
ከመቀለ ውጪ ያሉ ሰዎች ወዳጅ ዘመዶቻቸን ከ40 ቀናት በኋላ በስልክ ስለማግኘታቸው በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየጻፉ ይገኛሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሳምንታት ተቋርጦ የቆየባት መቀለ የአሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት ጀምራለች።
በክልሉ በበርካታ ስፍራዎች በኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ በደረሰው ጉዳት የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦ መቆየቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቆ ነበር።
የደረሰውን ጉዳት ጠግኖ ነዋሪዎች የአሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሲሰራ መቆየቱን አስታውቋል።
በዚህም መቀለ፣ አላማጣ፣ ማይጨው፣ መሆኒ፣ ሰቆጣ፣ ኲዊሀ እና አዲጉዶም ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ማድረግ እንደተቻለም ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ በመቀለ
ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አህመድ ትናንት በመቀለ ከተማ ተገኝተው ከአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ከከፍተኛ የጦር መኮንኖች ጋር ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በመቀለ በነበራቸው ወይይት ጦርነቱን ለመሩ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እና ሠራዊት አባላት ምስጋና አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ባደረጉት ወይይት የህወሓት ኃይሎች የሉት የሠራዊት ብዛት ወደ 80 ሺህ ይገመት እንደነበር ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከመቀለ እየሸሹ በነበሩ የህወሓት ኃይሎች ላይ ብቻ ሠራዊቱ ሮኬት መተኮሱን በንግግራቸው መካከል ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ከጉብኝታቸው በኋላ "በመቀሌ ተገኝቼ ከብሔራዊ መከላከያ ሠራዊታችን አዛዦች እና ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ውይይት አድርጌያለሁ። የቴሌኮም እና የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረታዊ አገልግሎቶች ከጥገና ሥራ በኋላ ተመልሰው እየቀጠሉ ነው።
"የመሠረተ ልማት መልሶ ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን፣ ሰብዓዊ እርዳታም እየቀረበ ነው። ወንጀለኛውን ቡድን ለሕግ የማቅረብ ሥራችን ይቀጥላል" ብለዋል።
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር ጉብኝት
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዶክ (ዶ/ር) የሥራ ጉብኝነት ለማድረግ ትናንት በኢትዮጵያ ተገኝተው ነበር።
ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንሰትር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት መሆኑን ቢጠቅሱም አብደላ ሀምዶክ ግን ከሠዓታት በኋላ በመጡበት ዕለት ወደ ሱዳን ተመልሰዋል።
ሱዳን ትሪቢዩን የአብደላ ሀምዶክ ፕሬስ ሴክሬታሪ፤ "የጠቅላይ ሚንሰትሩ የኢትዮጵያ ጉብኝት ፍሬያማ እና የጉብኝቱን ዓላማ ሙሉ በሙሉ ያሳካ ነበረ" እንዳሉት ዘግቧል።
መነሻ
ለዓመታት የቆውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ያጋጠመውን ቀውስ ተከትሎ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ከወሰኑ በኋላ የለውጥ ፍላጎቱ በገዢው ፓርቲ ውስጥ መንጸባረቅ ጀምሮ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ በህወሓት የበላይነት ሲመራ ነበረው ኢህአዴግ በሕዝቡ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለማብረድና የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለማድረግ መወሰኑ ይታወሳል።
በለውጡ ሂደት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በፓርቲው የተወሰነውን የለውጥ እርምጃ በፍጥነት በመተግበር ከአብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አድናቆትን ለማግኘት ችለዋል።
በእርማጃቸው የገፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአራት ብሔራዊ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው ኢህአዴግ በማክሰም አንድ ወጥ አገራዊ ፓርቲ ለመመስረት ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ የገዢው ፓርቲ ዋነኛ መስራችና በአገሪቱ አጠቃላይ ፖለቲካ ውስጥ ሰፊ ተጽእኖ የነበረው ህወሓት ቅሬታና ተቃውሞ ማሰማት ጀመረ።
"ብልጽግና" የተባለው ተለያዩ የክልል ፓርቲዎችን በማሳተፍ ከኢህአዴግ ሰፋ ያለ ፓርቲ ሲመሰረት ህወሓት ከፓርቲው እራሱን በማግለሉ መካሰስና ውዝግብ መከሰት ጀመረ። ከዚህም በኋላ የህወሓት አመራሮች ማዕከላቸውን መቀለ በማድረግ የተቃዋሚ ፓርቲነትን ሚና ይዘው ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።
ህወሓት የገዢነት መንበሩን ከኢህአዴግ ከተረከበው ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ልዩነት በማንሳት ሲወዛገቡ የቆዩ ሲሆን፤ በተለይ ባለፈው ዓመት መካሄድ የነበረበትና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ የተላለፈው ምርጫ ነገሮችን በከፍተኛ ደረጃ እንዲካረሩ ማድረጉ ይታወሳል።
በበሽታው ምክንያት የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች የስልጣን ዘመን ምርጫው አስኪደረግ ድረስ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ሲወሰን ህወሓት ግን "ሕገወጥ እርምጃ ነው" በማለት ተቃውሞውን አሰምቶ በትግራይ ክልል ግን የተናጠል ምርጫ እንደሚያካሄድ አሳውቆ ነበር።
ይህ የህወሓት ውሳኔ ከምርጫ ቦርድ፣ ከፌደራል መንግሥቱና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት "ተቀባይነት የለውም" በሚል ተቃውሞ ቢገጥመውም በክልሉ የምርጫ አስፈጻሚ አካል በማዋቀር ባለፈው ዓመት ጳጉሜ ወር ላይ መርጫው ተካሂዶ ህወሓት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ውጤት ማሸነፉ ተነግሮ ነበር።
ይህ የምርጫ ሂደት ቀድሞውንም ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር የነበረውን ውዝግብ እንዲካረር አደረገው። መጀመሪያም ምርጫው ተቀባይነት የለውም በማለት ሲያስጠነቅቅ የነበረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌደራል መንግሥቱ ከክልሉ መስተዳደር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳያደርግ በማዘዘዝ በጀት የማቀብ እርምጃ ወሰደ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በትግራይ ክልል የሚገኘውን ከአገሪቱ ሠራዊት ትልቁ ክፍል የሚባለውን የሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ማድረሳቸው የተነገረው።
ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በህወሓት ኃይሎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ በምድርና በአየር ለሦስት ሳምንታት ያህል የዘለቀ ዘመቻ ተካሂዶ የክልሉ ዋና ከተማ በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት እጅ ስትገባ መንግሥት ሕግ የማስከበር ያለው ወታደራዊ ዘመቻ ማብቃቱን ማሳወቁ ይታወሳል።