ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በናይጄሪያ በአጋቾች ተጠልፎ የነበረው ታዳጊ ተማሪ እንዴት ሊያመልጥ ቻለ?
የ17 ዓመቱ ተማሪ (ስሙን የማንገልፀው) በአጋቾች ከተጠለፉ ከ500 በላይ ታዳጊ ተማሪዎች አንዱ ነበር።
ተማሪዎቹ በሰሜን ምዕራብ ካሲና ግዛት ከሚገኘው ከአንድ የመንግሥት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አርብ ዕለት ነበር በአጋቾች ተጠልፈው የተወሰዱት።
"ይገፈትሩንና ይደበድቡን ነበር። ምሽቱን በጫካ ውስጥ እየተጓዝን ነው ያሳለፍነው። አንዳንዴ በእሾህ ላይ ነበር የምንሄደው። ሌሊቱ ወገግ ከማለቱ 30 ደቂቃ በፊት እንድንተኛ ታዘዝን" ይላል ተማሪው ያለፉበትን ስቃይ ሲያስታውስ።
ታዲያ በዚህ ጊዜ ነበር እንዴት ከአጋቾቹ ሊያመልጥ እንደሚችል የተረዳው።
አጋቾቹ እረፍት እያደረጉ ሳለ በአቅራቢያው አንድ ዛፍ ተመለከተ።
"አረፍ እንዳልን ወደ ኋላ በጀርባየ ተንጋለልኩ። መሬት ላይ ተኝቼ እግሮቼን ዘረጋሁ" ይላል። ከዚያም አየተሳበ ወደ ዛፉ ተጠግቶ ተከለለ።
እርሱ እንደሚለው ታጣቂዎቹ በእረፍት ላይ የነበሩትን ቀሪዎቹን ቡድኖች እንዲነሱ ትዕዛዝ ሲሰጡ። እርሱን ልብ አላሉትም ነበር።
ከዚያም ይላል ተማሪው፤ "ከዚያም ሁሉም እንደሄዱ በአቅራቢያ የሚገኝ መንደር እስከምደርስ ድረስ እንደ እባብ እየተሳብኩ አካባቢየን መቃኘት ጀመርኩ። በፈጣሪ እርዳታም ከእነርሱ ማምለጥ ቻልኩ" ይላል።
ተማሪው ትልቁ ዛፍ ፣ ፈጣን ውሳኔ እና ረዥም ርቀት በደረቱ እየተሳበ መሄዱ ከአጋቾቹ እንዲያመልጥ እንደረዱት ይናገራል።
የካሲና ግዛት ገዥ አሚኑ ብሎ ማሳሪ "ከታገቱት ተማሪዎች 333 ተማሪዎች አሁንም የት እንዳሉ አይታወቅም፤ ምን ያህሎቹም በጠላፊዎቻቸው እጅ እንደሚገኙም ግልፅ አይደለም። በርካቶች አምልጠው ሊሆን ቢችልም እስካሁን አልተገኙም።" ብለዋል።
ገዥው አክለውም ከአጋቾቹ ጋር ድርድር እየተካሄደ እንደሆነም ተናግረዋል።
የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ቃል አቀባይ ጋርባ ሸሁ በበኩላቸው፤ ከእገታው ያመለጡት ተማሪዎች 10 የሚሆኑ ጓደኞቻቸው ከታጣቂዎቹ ጋር እንደቀሩ እንደነገሯቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
"የፀጥታ አካላት እንደሆኑ ነበር የነገሩን"
ከእገታው ያመለጠው ተማሪ እንዳለው የታጠቁት ቡድኖች አርብ ዕለት ከምሽቱ 2፡30 ገደማ ነበር ወደ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ያመሩት።
በርካታ ተማሪዎች የተኩስ ድምፅ ሲሰሙ በትምህርት ቤቱ አጥር እየዘለሉ አመለጡ።
ሆኖም በታጣቂዎቹ በባትሪ እየተፈለጉና የፀጥታ አካላት እንደሆኑ እየተነገራቸው፤ በመታለል ወደ ትምህርት ቤታቸው ተመለሱ።
ተማሪዎቹ ቡድኖቹ እንደነገሯቸው የፀጥታ አካላት አለመሆናቸውን የተረዱት ከረፈደ ነበር።
ከዚያም ተማሪዎቹ በታጣቂዎቹ ተከበው በጫካ ውስጥ እንዲጓዙ ተገደዱ።
"ወደ ጫካ እንደተወሰድን አንደኛው እንድንቆም አዘዘንና ጉዟችንን ከመቀጠላችን በፊት ምን ያህል እንደሆንን ቆጠረን" ይላል ተማሪው።
ያኔ የተማሪዎቹ ቁጥር 520 እንደነበርና እርሱ ሲያመልጥ ግን በስፍራው ማንንም እንዳላየ ይናግራል።
መንግሥት በአካባቢው ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን ለጥቃቱ ተጠያቂ አድርጓል። እነዚህ ታጣቂዎች ብዙ ጊዜ በገንዘብ ለመደራደር ሲሉ ሰዎችን ያግታሉም ብሏል።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ የትውልድ ቦታ በሆነችው ካትሲና የደረሰው ጥቃትም መንግሥት በደህንነት ቁጥጥር ላይ ያለውን ቸልተኝነት ያሳየ ነው በሚልም ከፍተኛ ትችት እየደረሰባቸው ነው።
በሃምሌ ወር ቡድኑ ባወጣው ቪዲዮ ግዛቱን እያስፋፋ መሆኑንና በአገሪቷ ሰሜን ምዕራብ ክፍልም መግባቱን አስታውቋል።
በአካባቢው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መንግሥት "ሽፍቶች" አደረሱት ባሉት ጥቃቶች ተገድለዋል።
እነዚህ "ሽፍቶች የተባሉት የወንጀለኞች ቡድን ከቦኮ ሃራም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ይኑረው ግልፅ አይደለም።
ሆኖም ከአልቃይዳ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው የሚባለው አንሳሩ የተባለ ሌላ ቡድን በግዛቲቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይንቀሳቀሳል።
ቦኮ ሃራም ከ2009 ጀምሮ አስከፊ የሆነ የሽምቅ ውጊያ እያካሄደ ሲሆን በተለይም በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ በኩልም አትኩሮቱን አድርጓል ።
በዚህም ግጭት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል እንዲሁም ከሁለት ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችም ቤት ንብረታቸውን ትተው ተፈናቅለዋል።