ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቱርክ ከሩሲያ ሚሳኤል በመግዛቷ በአሜሪካ ማዕቀብ ተጣለባት
አሜሪካ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል የሆነችው ቱርክ ላይ ማዕቀብ ጣለች።
ቱርክ ማዕቀቡ የተጣለባት ባለፈው ዓመት ከሩሲያ እጅግ ውስብስብና ዘመናዊ የሚባል የሚሳኤል መቃወሚያ ሲስተም በመሸመቷ ነው።
አሜሪካ እንደምትለው ቱርክ ከሩሲያ የገዛችው ኤስ-400 ከመሬት ወደ አየር ተወንጫፊ ሚሳኤል ስርዓት (ሲስተም) ከኔቶ ስርዓት ጋር የሚግባባ ወይም የሚጣጣም አይደለም።
ይህም የአውሮጳ አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን ስጋት ላይ የሚጥል ነው።
የአሜሪካ ማዕቀብ በቱርክ ላይ የጦር መሳሪያ ግዥና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተጣለ ነው።
አሜሪካ ማዕቀብ መጣሏን እንደተሰማ ሞስኮና አንካራ ቅሬታቸውን ለማሰማት ጊዜ አልወሰዱም።
ቱርክ ዘመናዊ ሚሳኤል ስርዓት ከሩሲያ በመግዛቷ የተነሳ አሜሪካ ለቱርክ ከዚህ በኋላ ኤፍ-35 ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶችን ለመሸጥ ፍቃደኛ እንዳልሆነች አስታውቃለች።
የቱርክ ከሩሲያ ኤስ-400 የተሰኙ ከምድር ወደ አየር ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን መሸመት አሜሪካንን ያበሳጫት በሁለት ምክንያት እንደሆነ ተብራርቷል።
አንዱ ይህ መሳሪያ ከኔቶ አገሮች የሚሳኤል ስርዓት ጋር መጣጣም የሚችል አለመሆኑ ሲሆን በዋናነት ግን ቱርክ ግዢውን ከሩሲያ ስትፈጽም ወደ ሩሲያ መከላከያ ካዝና የሚገባው ጠቀም ያለ ገንዘብ የሩሲያ የመከላከያ ሠራዊትን ያጠናክራል የሚል ፍርሃት ነው።
የኔቶ አባል ቱርክ በሩሲያ ቴክኖሎጂ መታጠቋ ለጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱ አደጋ እንደሆነም አሜሪካ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ቱርክ ግዢውን እንዳትፈጽም ደጋግመን ብናስጠነቅቃም አልሰማ ብላለች ሲሉ ወቅሰዋል።
"አሁንም ቢሆን አጋራችን የሆነችው ቱርክ ይህንን የሚሳኤል ስርዓት በመተው ወደኛ እንድትመለስ እንጠይቃለን" ይላል በፖምፒዮ ስም የወጣው መግለጫ።
አዲሱ ማእቀብ የቱርክ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ዳይሬክቶሬት ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ደሚር እና ሌሎች ሦስት ባለሥልጣናት ላይ ጭምር የጉዞና የግዥ እንዲሁም የማይንቀሳቀስ ሀብታቸውን ጭምር ያገደ ማዕቀብ ነው።
ቱርክ ማዕቀቡ ተገቢ አለመሆኑን አውስታ ነገሮችን በንግግርና በዲፕሎማሲ ለመፍታት ጊዜው አልረፈደም ብላለች።
ሆኖም አሜሪካ በማዕቀቡ የምትገፋበት ከሆን ቱርክም በዚያው መጠን አሜሪካንን ትበቀላለች ብለዋል።
አንካራ እንደምትለው ይህን ዘመናዊ የሚሳኤል ስርዓት ከሩሲያ ለመግዛት የተገደደችው አሜሪካ ሰራሽ ሚሳኤሎችን ለመግዛት አመልክታ ፍቃድ በማጣቷ ነው።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቨ "የአሜሪካን በቱርክ ላይ የጣለችው ማዕቀብ ሌላ የአሜሪካ እብሪተኝነትና ማን አለብኝነት ማሳያ ነው" ብለውታል።
ቱርክ 30 አባላት ባሉት የሰሜን ጦር ቀል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ውስጥ ብዙ ጦር ያዋጣች 2ኛዋ አገር ናት።
ለአሜሪካ ወሳኝ አጋር ተደርጋ የምትወሰደው ቱርክ ከሶሪያ፣ ኢራቅና ኢራን ጋር የምትዋሰንና በጂኦግራፊ አቀማመጥ ወደር የማይገኝለት ስትራቴጂክ ቦታ ያላት አገር ናት።
የአሳድ ተቃዋሚዎች የጦር መሳሪያ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና የነበራት ቱርክ ከኔቶ አባል አገራት ጋር ተከታታይ ፖለቲካዊ ፍጥጫ ውስጥ መግባቷ ይታወሳል።
ኤርዶጋን በ2016 መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከተደረገባቸው ወዲህ አምባገነናዊና የቱርክ ብሔርተኝነትን የሚያቀነቅኑ ቆራጥ መሪ እየሆኑ መምጣታቸው በተለይ የአውሮጳ አጋሮቻቸውን ቅር ማሰኘቱ አልቀረም።
ቱርክ ከጎረቤቷ ግሪክ ጋር በዚህ ዓመት ወታደራዊ ፍጥጫ ውስጥ መግባቷ የሚዘነጋ አይደለም።