ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትግራይ ፡ ከ40 ቀናት በኋላ በመቀለ የስልክና የመብራት አገልግሎት መጀመሩ የፈጠረው ስሜት
በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በትግራይ ክልል የጸጥታ ኃይሎችና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ላለፉት 40 ቀናት በክልሉ የኤሌትሪክ፣ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ተቋርጠው ቆይተዋል።
በእነዚህ ጊዜያት በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች የስልክ፣ መብራት፣ ኢንተርኔት ባንክና የመሳሰሉት ለዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ወሳኝ የሆኑ አገልግለቶች ተዘግተው ከርመዋል።
ይህም ቢቢሲ በተለያየ ወቅት ያናገራቸው በክልሉ ውስጥ እንዲሁም በሌላ የአገሪቱ አካባቢና ከአገር ውጪ በሚኖሩ ላይ ሰዎች ላይ ጭንቀትና ከባድ ጫና ማስከተሉን ገልፀው ነበር።
ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም፣ የግንኙነት መስመሮች እንዲከፈቱና የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረግ የአቅርቦት መስመሮች አለገደብ ክፍት እንዲሆን ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ኢትዮ-ቴሌኮም ከትናንት በስተያ ቅዳሜ የስልክ አገልግሎት በትግራይ ዋና ከተማ መቀለ ላይ እንደጀመረ ቢገልጽም፣ የመብራት አገልግሎት በወቅቱ ባለመጀመሩ ጥቂቶች ብቻ በአገልግሎቱ ለመጠቀም ችለው ነበር።
ይሁን እንጂ፣ ከትናንት አመሻሽ 11 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ መብራት አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በከተማዋ ውስጥ ከሚገኙና ከትግራይ ክልል ውጪ ካሉ ዘመድ ወዳጆቻቸው ጋር መገናኘት ችለዋል።
በውጭ አገራት የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች በበኩላቸው፣ የቤተሰባቸው አባላትና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ለማወቅ ችለዋል።
በማኅበራዊ ሚድያ ላይ፣ በርካቶች ቤተሰቦቻቸውን ማነጋገራቸው በመግለጽ የተሰማቸውን ደስታ ሲገልጹ፣ አንዳንዶች ደግሞ በጦርነቱ ወቅት አልያም ከዚያ በኋላ የተጎዱ አልያም በተለያየ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ የቤተሰብ አባላቶቻቸውንና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን መርዶ እንደሰሙ ጽፈው ታይቷል።
"ጨላማ ውስጥ ነበርን"
አንድ ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የመቀለ ከተማ ነዋሪ "ከአንድ ወር በላይ የስልክና የመብራት አገልግሎት መቋረጡ ኑሯችንን አክብዶታል። በቀላሉ ከሰዎች ጋር ለመገናኘት ሆነ ሥራ ለመሥራት የማንችልበት ጨለማ ውስጥ ነው የቆየነው" ብሏል።
በአጋጣሚ ቀደም ብሎ ቀለብ የሸመተ ሰው ካልሆነ በስተቀር፣ እጁ ላይ ምንም ዓይነት ነገር ያልነበረው ግለሰብ እህል መሸመት ስለማይችል ከባድ ችግር ላይ ወድቆ እንደነበረም ጨምሮ ተናግሯል።
በተለይ የባንክ አገልግሎት ፈጥኖ ካልተጀመረ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል የሚሰጉ በርካቶች መሆናቸውን ቢቢሲ መረዳት ችሏል።
ቢቢሲ ያነጋገረው ይህ ወጣት ከተማዋ ስላለችበት ሁኔታም ሲያስረዳ "12 ሰዓት ላይ ወደ ቤት ለመግባት ተገደን ነበር። ከዚያ በኋላ ስለሚሆነው ነገር የምንሰማበት ሁኔታ አልነበረም። እሱን ለመስማት የግድ እስከ ጠዋት ድረስ መጠበቅ ይኖርብናል። ቴሌቪዥንና ሬድዮም በመብራት መጥፋት ምክንያት ስለማይሰሩ ምን እየተፈጸመ እንደሆነ ማወቅ አንችልም ነበር" በማለት ይገልጻል።
ቢቢሲ መቀለ ከተማ ስላለው ሁኔታ ለመጠየቅ የደወለለት ሌላ ግለሰብ "አንተ ሰው ከሰላምታ ውጪ ሌላ ነገር እንዳታናግረኝ፤ እንዳትጠይቀኝ" በሚል ለደኅንነቱ እንደሚሰጋ ገልጿል።
በዚህም የተነሳ መቀሌ በህወሓት ስር በነበረችበት ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ ስላለው፣ ስለ ሰማውና ስለተመለከተው ነገር ለቢቢሲ ለመናገር አልደፈረም።
ከመቀለ ውጪ- ስጋትና ጭንቅ
በርካቶች በከተማዋ የስልክና የመብራት አገልግሎት በመጀመሩ ደስተኞች ቢሆኑም፣ ከከተማዋ ውጪ በክልሉ ያሉ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ማወቅ ባለመቻላቸው መጨነቃቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ጀምሮ በምዕራብ ትግራይ ሑመራ፣ ዳንሻና በመሳሰሉት እንዲሁም በደቡብ ትግራይ በአላማጣ ከተሞች አካባቢ የስልክ አገልግሎቱን መስጠት መጀመሩ መገለጹ ይታወሳል።
በተቀሩት የትግራይ ክልል ከተሞች ግን እስከአሁን የግንኙነት መንገድ ዝግ በመሆኑ የተነሳ ሕዝቡ ያለበት ሁኔታ እንደሚያስጨንቃቸው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች ገልፀዋል።
በተለይ ደግሞ ከባድ ጦርነት በተካሄደባቸውና "እየተካሄደባቸው ነው በሚባሉ ከተሞች" የቤተሰባቸው ሁኔታ እንደሚያስጨንቃቸው ተናግረዋል።
ቢቢሲ ካነጋገራቸው ግለሰቦች መረዳት እንደቻለው በክልሉ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ያልተጀመረ ሲሆን፣ በአብዛኛው ከከተማ ወደ ከተማ ተንቀሳቅሰው ወዳጅ ዘመዶቻቸው ያሉበትን ሁኔታ መጠየቅ ሆነ ማወቅ እንዳልቻሉ አስረድተዋል።
አንዳንዶቹ ግን በተለያዩ አቅራቢያ ከተሞች ስላሉ ቤተሰባቸው ሁኔታ ለማወቅ እንደቻሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የስልክና የኢንትርኔት አገልግሎቶች ለሳምንታት ተቋርጠው በመቆየታቸው የተነሳ በፌደራል መንግሥትና በህወሓት መካከል ወታደራዊ ግጭቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ፣ በክልሉ በትክክል ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ አልተቻለም።
ቢቢሲም ከየትኛውም ወገኖች ሲሰጡ የነበሩ መረጃዎችን ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
በኢትዮጵያ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጠው ብቸኛው ተቋም ኢትዮ ቴሌኮም በትግራይ ክልል ተቋርጦ የቆውን አገልግሎቱን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ ላይ እንዳለው የክልሉ ታጣቂ ኃይሎች በሽረ እና በመቀለ የሚገኙትን ማዕከላት የኃይል አቅርቦት ሆን ብለው በመቋረጣቸው መሆኑ ተገልጿል።
ጨምሮም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ባሉ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት በመፈጸሙ እነዚህን በመጠገን በቅርብ ቀናት ውስጥ አጠቃላይ ክልሉ አገልግሎቱ እንደሚጀመር ተነግሯል።
ሌሎች እንቅስቃሴዎች
በፌዴራል መንግሥት የተሰየመው በሙሉ ነጋ (ዶ/ር) የሚመራው የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ሰሞኑን ሥራ መጀመሩን ያሳወቀ ሲሆን በተለይ በሽረ ከተማ አዲስ ከንቲባ መሾሙን አሳውቋል።
ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ ተቋርጦ የቆየው የመንግሥት መደበኛ ሥራ እንዲጀመርና የመንግሥት ሰራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ አሳውቋል።
የጤና ማዕከላት በከተማዋ ሆነ በክልሉ መሠረታዊ የህክምና አገልግሎት በማይሰጡበት ደርጃ ወርደው እንደነበር ሲገለጽ የቆየ ቢሆንም ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር በበኩሉ ወደ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል መድኃኒት ማጓጓዙን ተገልጿል።
የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ ሰሞኑን በአንዳንድ የክልሉ ከተሞች ላይ እርዳት ማድረሱን ገልጿል።