ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትግራይ፡ የኖርዌይ ተራድኦ ድርጅት ወደ ሱዳን የገቡ ስደተኞች በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናገረ
የኖርዌ የስደተኞች ካውንስል (ኖርዌጂያን ሬፊውጂ ካውንስል) ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ግችቱን እየሸሹ የሚገኙ ስደተኞች እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ አለ።
በየዕለቱ ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ከሚሸሹት በሺዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ነፍሰ ጡር እናቶች፣ በእድሜ የገፉ በሽተኛ አዛውንቶች እና በግጭቱ ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው የተነጣጠሉ ሰዎች ይገኙባቸዋል ብሏል ድርጅቱ።
"ምንም አይነት መጠለያ የለም ብርድ ልብስ ብቻ ነው ያለው። በቂ ባይሆንም የመጠጥ ውሃ እና ምግብ ለስደተኞች እየቀረበ ነው። ይሁን እንጂ መጸዳጃ ቤት፣ ገላ መታጠቢያ ቦታ እና የጤና አገልግሎት የለም። ስደተኞቹ በጀርባቸው ተሸክመው ካመጡት ነገር ውጪ ምንም የላቸውም" ሲሉ የኖርዌይ የስደተኞች ካውንስል የሱዳን ዳይሬክተር ዊል ካርተር ተናግረዋል።
ድርጅቱ እስከ 5 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በየዕለቱ ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን እየተሻገሩ መሆኑን ጠቅሶ፤ በገዳሪፍ ግዛት ኡም ራቁባ በተባለው የስደተኞች መጠለያ ካምፕስደተኞቹን ለመርዳት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሷል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሆነ በፌደራል መንግሥቱ እና ትግራይን በሚያስተዳድረው ህውሓት መካከል በተከሰተው ግጭት እስካሁን ወደ ሱዳን የሸሹ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ30 ሺህ በላይ ሆኗል።
"በመጠለያ ጣቢያው ነብሰ ጡር እናቶች ይገኛሉ። መድኃኒት በሌለበት የስኳር በሽተኞች አሉ። የሕክምና ድጋፍ በሌለበት ኤችአይቪ/ኤድስ በደማቸው ያለ ሰዎች አሉ። ይህ ለበርካቶች እጅግ አስጨናቂ ወቅት ነው" ሲሉ ዊል ካርተር ተናግረዋል።
የደርጅቱ የሱዳን ዳይሬክተር ጨምረው እንደተናገሩት፤ ወደ ሱዳን እየገቡ ካሉ ስደተኞች መካከል በጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንደሚገኙ ገልጸዋል።
"ጉዳት የደረሰባቸው አሉ። ድንበር መሻገሪያ አቅራቢያ ሕክምና ያገኙ አሉ። የግንኙነት አገልግሎት በመቋረጡ ሰደተኞቹ ዘመዶቻቸውን ማግኘት ባለመቻላቸው በእጅጉ ተጨንቀዋል። ሌሎች ደግሞ በግጭቱ ምክንያት ሰዎች ሲሞቱና ሲፈናቀሉ ማየታቸው ነግረውናል" ብለዋል።
የኖርዌይ የስደተኞች ካውንስል ተፈናቃዮች የሚያስፈልጓቸውን መሰረታዊ ቁሳቁስ ከአካባቢው ገበያ ለመግዛት ይረዳቸው ዘንድ የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አስታውቋል።
ድጋፍ አድራጊ አካላትም የሱዳን መንግሥት ለስደተኞች ድጋፍ እንዲያደርግ የበኩላቸውን እንዲወጡ የስደተኞች ካውንስሉ ጠይቋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በየዕለቱ እስከ 6ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ጦርነቱን በመሸሽ ወደ ሱዳን ይሻገራሉ ሲል ግምቱን አስቀምጧል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ከቀናት በፊት ላይ በጦርነቱ ምክንያት የሚፈናቀሉ ንሑሃን ዜጎችን ለመቀበል መንግሥታቸው ዝግጁ መሆኑን አስታውቀው ነበር።
በዚህም "ወደ ጎረቤት አገራት የሚሸሹ ዜጎችን ለመቀበል፣ ንብረታቸውን ለመጠበቅ እና አስፈላጊ የሆነው የሰብዓዊ እርዳታ በአገር መከላከያ በኩል እንደሚደረግ እና ወደ ቀያቸውም ሲመለሱ ሰላማቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ" ጠቅላይ ሚንስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፈረዋል።
በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን በሚመራው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው ፍጥጫ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በተናጠል የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ መባባሱ ይታወሳል።
በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ በክልሉ ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸውን ተከትሎ ፍጥጫው ወደ ግጭት አምርቶ ሁለት ሳምንት አልፎታል።
በዚህም ሳቢያ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች ግጭቱን በመሸሽ ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን የተሰደዱ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ያስታወቀ ሲሆን አሃዙ በየዕለቱ እጨመረ መምጣቱን የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እገለጹ ነው።