ትግራይ፡ በባሕር ዳር ከተማ ላይ ዳግም የሮኬት ጥቃት ተፈጸመ

ትናንት ሐሙስ ለዛሬ አርብ አጥቢያ ከእኩለ ሌሊት በኋላ በባሕር ዳር ከተማ ላይ ዳግም የሮኬት ጥቃት መፈጸሙን ነዋሪዎችና የክልሉ መስተዳደር ገለጹ።

በስፍራው የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢም ትናት ሌሊት ኅዳር 10/2013 ዓ.ም ከእኩለ ሌሊት በኋላ 7 ሰዓት ከ30 ገደማ ላይ የሮኬት ፍንዳታ በከተማዋ መሰማቱን አረጋግጧል።

ቢቢሲ የዚህ የሮኬት ጥቃት ዒላማ ምን እንደነበረ እና በጥቃቱ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ እስካሁን ማረጋገጥ አልቻለም።

የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት በበኩሉ ሌሊት 7 ሰዓት ከ40 ላይ በባሕር ዳር የሮኬት ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጦ ጥቃቱን ያደረሰው ህወሓት ነው ሲል ከሷል።

አርብ አመሻሽ ላይ የትግራይ ኃይሎች ቃል አቀባይ እንደሆኑ የተነገረላቸው ገብረ ገብረጻድቅ በባሕር ዳር ከተማ ላይ የተፈጸመውን የሮኬት ጥቃት መፈጸማቸውን አረጋግጠው፤ ጥቃቱ ኢላማውን መትቶ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

የአማራ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ በጥቃቱ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ዘግቧል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ይልማ መርዳሳ ስለሮኬት ጥቃቱ ለሸገር ሬዲዮ እንደተናገሩት በጥቃት የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አመልክተዋል።

ሜጀር ጀነራል ይልማ ጨምረውም "የመጨረሻ ሞት ስለሆነ ወደ ሕዝብ ነው የተኮሱት ግን የደረሰ ምንም ጉዳት የለም። ጫካ ላይ ነው የወደቀው። እዚያ አከባቢም ሰው አልነበረም" ብለዋል።

የአየር ኃይል አዛዡ ለተፈጸመው ጥቃት "በአጭር ጊዜ ውስጥ አጸፋዊ እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ መናገራቸው ተዘግቧል።

ሐመስ ከዕኩለ ሌሊት በኋላ በባሕር ዳር ከተማ ላይ የተፈጸመው ጥቃት በከተማዋ በሚገኘው አየር ማረፊያ አካባቢ በሚገኝ የእርሻ ቦታ ላይ እንዳረፈ የቢቢሲ ዘጋቢ ወደ ስፍራው ሄዶ ተመለክቷል።

የሮኬት ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ኮንጣይነህ እና አርሶ አደር አትንኩት ካሴ ጥቃቱን በተመለከተ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከእንቅልፋቸው በከባድ ፍንዳታ መንቃታቸውን ገልጸው "ስንወጣ ግን አዝመራችንን በልቶት አገኘነው" ብለዋል።

የተተኮሰው ሮኬት በእርሻ መሬት ላይ የወድቀ መሆኑን አርሶ አደሮቹ የተናገሩ ሲሆን፤ የክልሉ ኃላፊዎችም ጥቃቱ በእርሻ ሜዳ ላይ በመውደቁ በሰው ላይ ጉዳት አላደረሰም ብለዋል።

በተመሳሳይ ከአንድ ሳምንት በፊት ማለትም ኅዳር 3 ሌሊት ላይ በባሕር ዳር እና በጎንደር ከተሞች ውስጥ የሚገኙትን አየር ማረፊያዎችን ኢላማ ያደረጉ የሮኬት ጥቃቶች መፈጸማቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም ተመሳሳይ ጥቃት በጎረቤት አገር በኤርትራ ዋና ከተማ አሥመራ ላይ የሮኬት ጥቃት መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን ስለጥቃቱም ሆነ ስላደረሰው ጉዳት ከኤርትራ መንግሥት የተሰጠ ዝርዝር ማብራሪያ የለም።

የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳም በእነዚህ ከተሞች ላይ የሮኬት ጥቃቶቹን መፈጸማቸውን በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው አረጋግጠው ነበር።

በትግራይ ክልል ላይ የተጣለውን የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት መረጃ የሚሰጠው ጽህፈት ቤት በወቅቱ እንዳስታወቀው የሮኬት ጥቃቱ በአውሮፕላን ማረፊያዎቹ አካባቢ "መጠነኛ ጉዳት" ደርሷል ብሎ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትግራይ ቴሌቪዥን ትናንት ተፈጽሟል በተባለ የአየር ጥቃት ጉዳት ደርሶባቸዋል ያላቸውን የሰዎች ምስል አሳይቷል።

ይህ ግን በገለልተኛ አካል ግን አልተረጋገጠም።

የፌደራል መንግሥቱም በዚህ ጉዳይ የሰጠው ማብራርያ የለም።

የክልሉ መንግሥት ከዚህ ቀደም በነበሩ የአየር ጥቃቶች ንጹሃን ሰዎች ተጎድተዋል ቢልም የፌደራል መንግሥቱ ግን የአየር ጥቃት ኢላማዎች ወታደራዊ ማእከላት ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ይላል።

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን በሚመራው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው አለመግባባትና መካሰስ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በተናጠል የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ መባባሱ ይታወሳል።

በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ በክልሉ ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸውን ተከትሎ ፍጥጫው ወደ ግጭት አምርቶ አሁን ሁለት ሳምንት አልፎታል።