ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትግራይ፡ የባሕርዳርና የጎንደር አየር ማረፊያዎችን ኢላማ ያደረገ የሮኬት ጥቃት ተፈፀመ
ትናንት ምሽት በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር እንዲሁም በቅርብ ርቀት በምትገኘው የጎንደር ከተማ ውስጥ የሚገኙ አየር ማረፊያዎችን ኢላማ ያደረገ የሮኬት ጥቃት መፈጸሙን የኢትዮጵያ መንግሥት ገለጸ።
በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ በክልሉ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት መረጃ የሚሰጠው ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው በሮኬት ጥቃቱ በአውሮፕላን ማረፊያዎቹ አካባቢ "መጠነኛ ጉዳት" መድረሱን አመልክቷል።
ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኘው ህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ጥቃቱን መፈጸማቸውን ለትግራይ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው የፌደራል መንግሥት አየር ኃይል በተለያዩ የትግራይ ከተሞች ላካሄደው የአየር ጥቃት "አጸፋዊ ምላሽ" በባሕር ዳርና ጎንደር አየር ማረፊያዎች ላይ "የሚሳኤል ጥቃት" መፈጸሙን አረጋግጠዋል።
ከዚህ ቀደምም የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ "ትግራይን ለማጥቃት የሚውል አየር ማረፊያ. . . የጥቃት ዒላማ እንደሚሆኑ" እንደተነገረ ዘግቦ ነበር።
ትናንት አርብ ማታ ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ በባሕር ዳር ከፍተኛ የተኩስና የፍንዳታ ድምጽ መሰማቱን በስፍራው የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ የገለጸ ሲሆን፤ የክልሉ መንግሥት ስለክስተቱ መግለጫ እስከሚያወጣ ድረስ በከተማው ነዋሪ ዘንድ ግራ መጋባት ተፈጥሮ እንደነበር ገልጿል።
ሮይተርስ በበኩሉ አንድ ባለስልጣንን ጠቅሶ ወደ ጎንደር አየር ማረፊያ የተተኮሰው ሮኬት አየር ማረፊያውን ላይ የተወሰነ ጉዳት ሲያደርስ፣ ወደ ባሕር ዳር ላይ የተተኮሰው ግን ከአየር ማረፊያው ውጪ መውደቁን ዘግቧል።
የአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምሽት 5:00 ሰዓት ላይ በክልሉ መገናኛ ብዙኀን በኩል እንዳስታወቀው በባሕር ዳር ከተማ በተለምዶ መኮድ በሚባለው አካባቢ እና ጎንደር ከተማ አዘዞ አካባቢ የተከሰቱ ፍንዳታዎች መኖራቸውን አስታውቆ ነበር።
እንደ ክልሉ መንግሥት መረጃ ከሆነ ፍንዳታው በጸጥታ ኃይሉ በፍጥነት በቁጥጥር ስር ውሏል።
አርብ ምሽት ሁለት ከፍተኛ ፍንዳታዎች በተከታታይ መሰማታቸውን የባሕር ዳሩ የቢቢሲ ዘጋቢ ያረጋገጠ ሲሆን፤ ከሁለቱ ፍንዳታዎች በኋላም በግምት እስከ 5፡20 ድረስ የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር።
በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ፍንዳታውን ተከትሎ መብራት ጠፍቶ ወዲያ የመጣ ሲሆን ዘግየት ብለው አገልግሎቱ የተመለሰባቸው ቦታዎችም እንደነበሩና ነገር ግን የክልሉ ኮምዩኒኬሽን የተፈጠረው የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ከሌላው ጊዜ የተለየ እንዳልሆነ አመልክቷል።
ባሕር ዳር ዛሬ ከጠዋቱ ጀምሮ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ መመለሷን ሪፖርተራችን ጠቅሶ፤ ትናንት ምሽት ከተከሰተው ፍንዳታ አንጻር ምንም የተለየ ነገር በከተማዋ የማይስተዋል መሆኑንና በከተማዋ የተለመደው የሰዎችና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መቀጠሉን ገልጿል።
ትናንት እኩለ ለሊት ላይ የአማራ ክልል መንግሥት ባስተላለፈው መልዕክት ፍንዳታው በትግራይ ክልል እተካሄደ ካለው ግጭት ጋር ይገናኝ አይገናኝ እየተጣራ ነው ያለ ቢሆንም፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢሮው ግን ጉዳዩ በቀጥታ የክልሉን መንግሥት ከሚመራው አካል ጋር እንደሚገናኝ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።
ቢሮው በተጨማሪ እንዳስታወቀው በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት መርማሪ ቡድን ተመድቦ እያጣራ መሆኑን ገልጾ በቀጣይ ይገለፃል ተብሏል።
ከሳምንት በፊት ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙ ከተነገረ በኋላ በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል ኃይሎች በመካከል በተቀሰቀሰው ውጊያ የአማራ ክልልን ከትግራይ ጋር በሚያዋስኑት አካባቢዎች ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ደረጃ እየተካሄዱ መሆኑ ይታወቃል።
ጦርነት ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሸሹ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኀን ዜጎችም ወደ ሱዳን መሸሻቸውን የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ድርጅት አስታውቋል።
በሁለቱ ከተሞች የተፈጸሙት ጥቃቶችን በተመለከተ የአማራ ክልልም ሆነ የፌደራሉ የአስቸኳይ ጊዜ የመረጃ ማዕከልና በክስተቱ ላይ እየተደረገ ያለው ምርመራ ሲጠናቀቅ ዝርዝሩ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።