ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትግራይ፡ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህወሓት ናቸው ያላቸውን የ34 ተቋማት የባንክ አካውንት አሳገደ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህወሓት የንግድ ድርጅቶች ናቸው በተባሉ ከሰላሳ በላይ የሚሆኑ ተቋማት የባንክ አካውንት ላይ ዕግድ እንዲጣልባቸው ማስድረጉን ገለጸ።
ዐቃቤ ሕግ እንዳለው ድርጅቶቹ የአገሪቱን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት "በኃይል ለመናድ ከሚንቀሳቀሰው ከህወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው" በማለት በሌሎች ድርጊቶች ውስጥ እንደሚሳተፉ ገልጿል።
በተጨማሪም ተቋማቱን ዘር ተኮር ጥቃትና የሽብር ድርጊት እንዲፈጸም የገንዘብ ድጋፍ በማቅረብ፣ በመመሳጠር፣ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ በግብር ስወራና የሙስና ወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ስለመሳተፋቸው ምርመራ ለመጀመር የሚያስችል በቂ ማስረጃ እንደተገኘባቸው ዐቃቤ ሕግ ባወጣው መግለቻ ላይ ጠቁሟል።
በዚህ የዐቃቤ ሕግ እርምጃ የ34 የህወሓት ድርጅቶች በአገሪቱ ውስጥ ባሉ በሁሉም ባንኮች ውስጥ ያላቸው ገንዘብ እንዲሁም የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይ እገዳ እንዲጣል አስደርጓል።
ይህ እርምጃ አስፈላጊ የሆነውም ተቋማቱ ሀብታቸውን ለማሸሽ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆኑ በቂ ማስረጃ በመቅረቡ ንብረቶች ሳይሸሹ ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ውሳኔ እስኪሰጥባቸው ድረስ ተገቢው ቁጥጥር ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
ዕግዱ የተጣለባቸው የምርትና የንግድ ተቋማት ሲሆኑ በፋይናንስ፣ በማዕድን፣ በጨርቃጨርቅ፣ በግንባታ፣ በጅምላ ንግድ፣ በትራንስፖርት፣ በፋብሪካ ምርቶችና በመሳሰሉት ዘርፎች የተሰማሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ ከህወሓት ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንዳላቸውቸው ሲነገር የቆዩ ድርጅቶች ናቸው።
ከእነዚህም መካከል በአገሪቱ ካሉ ትላልቅ የግንባታ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ሱር ኮንስትራክሽን፣ በአስመጪነትና በጅምላ ንግድ የሚታወቀው ጉና የንግድ ሥራዎች ድርጅት፣ የጨርቃ ጨርቅ አምራቹ አልምዳ፣ የሲሚንቶ ፋብሪካው መሰቦ፣ በትራንስፖርትና በውጪ ንግድ ላይ ተሰማርቶ የቆየው ትራንስ ኢትዮጵያ ተጠቅሰዋል።
በተጨማሪም መድኃኒት አምራቹ አዲስ ፋርማሱቲካል፣ ማዕድን አውጪው ኢዛና ማዕድን፣ የከባድ ተሽከርካሪዎች አካልን የሚያመርተውና የሚገጣጥመው መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ፣ የአገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማራው ሠላም የሕዝብ ማመላለሻ ማኅበር፣ የህትመት ሥራዎችን የሚሰራው ሜጋ ማተሚያ ድርጅት ይገኙባቸዋል።
ከእነዚህ በተጨማሪም ሌሎች በርካታ የንግድና የአገልግሎት ድርጅቶች የባንክ አካውንት ነው እንዳይንቀሳቀስ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያሳገደው።
እነዚህ ተቋማት በአገሪቱ ውስጥ በምርትና በአገልግሎታቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ሲሆን፤ የድርጅቶቹን አካውንት የመዝጋት እርምጃ የተወሰደው መንግሥት በህወሓት በሚመሩት የትግራይ ልዩ ኃይሎች እርምጃ መውሰድ ከጀመረ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው።
በህወሓት በሚመራው የትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የፌደራል ሠራዊት ላይ ጥቃት ፈፅሟል መባሉን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በክልሉ ልዩ ኃይል ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል።
የህወሓት ናቸው በተባሉት በእነዚህ የምርትና የአገልግሎት ድርጅቶች ላይ ከተወሰደው እርምጃ ቀደም ብሎ ዐቃቤ ሕግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በነበሩ የህወሓት አባላትን ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ተደርጓል።
በተጨማሪም የድርጅቱን ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በመከላከያ፣ በፌደራልና በክልሉ የፖሊስ ኃይል ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ 96 የሚደርሱ ግለሰቦችን የመያዣ ትዕዛዝ ማውጣቱ ይታወሳል>