ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትግራይ ፡ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ያለመከሰስ መብት ተነሳ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አራተኛ መደበኛ ስብሰባ የህወሓት ከፍተኛ አመራር አባላትን ጨምሮ የምክር ቤቱ አባላት የሆኑ የሰላሳ ስምንት (38) ግለሰቦችን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ተገለጸ።
ምክር ቤቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በተለያዩ ወንጀሎች የጠረጠራቸውን የእነዚህን ግለሰቦች ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ነው የውሳኔ ሐሳቡ በሙሉ ድምጽ ያፀደቀው።
በዚህም መሰረት የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትና የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን (ዶ/ር) ጨምሮ የ38 ግለሰቦች ያለመከሰስ መብት ተነስቷል።
ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ከተደረገባቸው ግለሰቦች መካከል የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የሆኑት አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ፣ አቶ አባይ ፀሐዬ፣ ዶክተር አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ አፅበሃ አረጋዊ፣ አቶ ገብረ እግዚአብሄር አርአያ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
ዐቃቤ ሕግ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የጠየቀባቸው ግለሰቦች በተለያዩ ወንጀሎች ስለተጠረጠሩ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ እነዚህም "ከፍ ያለ የአገር ክህደት በመፈጸም፣ በሕገ-መንግስቱና በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ በተደረገ ወንጀልና የጦር መሳሪያ ይዞ ማመፅ" ተጠቅሷል።
በተጨማሪም "የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት በሚፈጸም ወንጀል፣ የአገር መከላከያ ኃይልን በመጉዳት እና በሽብር ወንጀል በመሳተፍ እንዲሁም ዋና የሽብር አቅራቢ በመሆን" በመጠርጠራቸው መሆኑ ለምክር ቤቱ ተገልጿል።
ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው 38ቱም ግለሰቦች የትግራይ ክልልን በመወከል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው የቆዩ ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ የፌደራል መንግሥት የትግራይ ክልልን በሚመራው ህወሓት አማካይነት በሰሜን ዕዝ ስር በሚገኘው የአገሪቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅሶ "ሕግን ማስከበር" ያለውን ወታደራዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ይታወቃል።
በዛሬው ዕለት በአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው ትግራይን የሚያስተዳድረው የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ሲሆኑ ለወራት ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር በውዝግብ ውስጥ ቆይተዋል።
በተለይም በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ የተደረገውን አገራዊ ምርጫ በመቃወም በትግራይ ክልለ ክልላዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረጋቸው በሁለቱ አካላት መካከል የነበረውን አለመግባባት አባብሶታል። የተደረገውን ክልላዊ ምርጫ የፌዴሬሽን ምክር ቤት "ሕገወጥና ተፈጻሚነት የሌለው" በማለት ውድቅ ያደረገው ሲሆን በክልሉ መስተዳደር ላይ ተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱም ይታወሳል።
የፌደራል መንግሥቱ ሕግ ማስከበር ባለውና ከሳምንት በፊት በክልሉ ባሉ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተከትሎ በትግራይ ክልል ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመታወጁ በተጨማሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም መወሰኑ ይታወሳል።