ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ላይ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፀደቀ
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት መሰብሰቢያ አደራሽ አካሂዶ፤ ትናንት የሚኒስትሮች ምክር በትግራይ ክልል ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጽድቋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ ጥቅምት 25፣ 2013 ዓ. ም. ባደረገው አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ መንግሥት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን አስታውቋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት መግለጫ አክሎም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ እንደሚሆን አስታውቆ፤ ይህንን አዋጅ የሚያስፈፅም በኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተወጣጡ አባላት ያሉት ግብረ ኃይል መቋቋሙን ገልጿል።
ግብረ ኃይሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን ‘‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ሀይል’’ ተብሎ እንደሚጠራም ተነግሯል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መደንገግ ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያስረዳም፤ የሀገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብንና የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ እና ሀገሪቷን ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚወስዱ ማናቸውንም ድርጊቶችን የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጿል።
ይህን ሁኔታ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን የጠቆመው መግለጫው፤ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ልዩ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ እና ተግባራዊ በማድረግ ሁኔታውን መቆጣጠር በማስፈለጉ አዋጁ መታወጁን ገልጿል።
አዋጁ በመላው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ለስድስት ወራት ተፈፃሚ የሚደረግ ሲሆን፤ እንደያስፈላጊነቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚ ወይም ቀሪ የሚሆንባቸውን ተጨማሪ አካባቢዎችነ ግብረ ኃይሉ በሚያወጣው በመመሪያ ይወስናል ተብሏል።