ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ
የኢፌዴሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ።
የኢፌድሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ፣ ጥቅምት 25/2013 ባደረገው አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ መንግሥት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን አስታውቋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት መግለጫ አክሎም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ እንደሚሆን አስታውቆ ይህንን አዋጅ የሚያስፈፅም በኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተወጣጡ አባላት ያሉት ግብረኃይል መቋቋሙን ገልጿል።
ግብረኃይሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን "የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረሀይል" ተብሎ ይጠራልም ተብሏል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መደንገግ ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያስረዳም የሀገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብንና የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ እና ሀገሪቷን ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚወስዱ ማናቸውንም ድርጊቶችን የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጿል።
አክሎም በትግራይ ብሔራዊ ክልል ውስጥ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲሁም የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥሉ በተለይም የአገርን ሉዐላዊነት የሚገዳደሩ፣ የፌደራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በክልሉ እንዳይወጣ እና ሀገሪቷን የጦር አውድማ የሚያደርጉ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎችን ጭምር በመጣስ በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት እየተፈፀሙ ናቸው ብሏል።
ይህን ሁኔታ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን የገለፀው መግለጫው በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ልዩ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ እና ተግባራዊ በማድረግ ሁኔታውን መቆጣጠር በማስፈለጉ አዋጁ መታወጁን ገልጿል።
አዋጁ በመላው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ተፈፃሚ የሚደረግ ሲሆን፣ እንደያስፈላጊነቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚ ወይም ቀሪ የሚሆንባቸውን ተጨማሪ አካባቢዎችነ ግብረኃይሉ በሚያወጣው በመመሪያ ይወስናል ተብሏል።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በ2/3ኛ ድምፅ መፅደቅ አለበት።