ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ኩባንያዎች ከቻይና ወታደራዊ ተቋማት ጋር እንዳይሰሩ አገዱ
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ኩባንያዎች ከቻይና ወታደራዊ ተቋማት ጋር እንዳይሰሩ የሚያግድ አዲስ ትዕዛዝ አወጡ።
በዚህም መሰረት ማንኛውም የአሜሪካ ኩባንያ ከቻይና መከላከያ ጋር ያለውን የሥራ ግንኙነት እንዲያቋርጥ አዝዘዋል። ከዚህም በተጨማሪ በቻይና መከላከያ የሚደገፉ ኩባንያዎቸ ላይ የአሜሪካ ኩባንያዎች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዳያፈሱ ያግዳል።
ትራምፕ ለዚህ ልዩ ትዕዛዝ መውጣት ዋንኛው ምክንያት ነው የሚሉት ቻይና የአሜሪካ ኩባንያዎችን እየተጠቀመችባቸው ነው የሚል ነው።
እንዴት ለሚለው ሲያብራሩ ቻይና ከአሜሪካ ኩባያዎች ጋር የተለያዩ የሥራ ስምምነቶች በመፈራረም መከላከያዋን እየገነባችም ነው። የቻይና መከላከያን የሚያዘምኑት የኛው የአሜሪካዊያን ኩባንያዎች ናቸው ብለዋል።
ይህ የትራምፕ እቀባ ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው ከፈረንጆቹ የጃንዋሪ ወር በኋላ ነው።
ይህ እቀባ የቻይና ሕዝብ ይደጉማዋል የሚባሉትን የቻይና ቴሌኮምን እንዲሁም ሂክቪሽን የቴክኖሎጂ ድርጅት ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል ተብሏል።
ዶናልድ ትራምፕ ያለፉትን አራት ዓመታት አገራቸው ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት ለመገደብ ብዙ ሲጥሩ ከርመዋል።
ትራምፕ ከቻይና በሚመጡ ገቢ እቃዎች ላይ ጫን ያለው ግብር በመጣል በቢሊዯን ዶላር ለመሰብሰብ ሞክረዋል። እንደ ቲክቶክ ያሉ የቻይና ግዙፍ ቴክኖሎጂ ላይ በአሜሪካ ምድር አገልግሎት እንዳይሰጡ የደኅንነት ስጋትን በማንሳት እቀባን ጥለዋል።
ቻይና በሆንግ ኮንግ ላይ እየወሰደችው ባለው ጥብቅ የቁጥጥር እርምጃ እንዲሁም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አነሳስና ሥርጭት የሁለቱ የዓለም ልዕለ ኃያላን ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲሻክር ካደረጉ ተጨማሪ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።
የትራምፕ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ይህ አዲስ ደንብ በዋይት ሐውስ ለወራት ሲብሰለሰል የነበረ ነው። በቻይና መከላከያ ይደገፋሉ፣ የተባሉ 31 የሚሆኑ የቻይና ኩባንያዎችም በስም ከተለዩ ቆይተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ይህ ያወጡት አዲስ እቀባ ተግባራዊ መሆን በጀመረ በ20 ቀናት ውስጥ ዋይት ሐውስን ይለቃሉ።