ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ምርጫ፡ በኮቪድ ያልተያዙት ማይክ ፔንስና ካማላ ሐሪስ ዛሬ ሌሊት ይፋጠጣሉ
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኮቪድ-19 ታመዋል። ኧረ እንዲያውም በርትተዋል ይላሉ ሐኪሞቻቸው፡፡ እሳቸው ብርቱ ነኝ ለማለት ሆስፒታል ጥለው እስከመውጣት ደርሰዋል፡፡ ለትራምፕ መሸነፍ ሞት ነው፡፡
በ74 ዓመታቸው ኮቪድን አሸንፈው ከሰሞኑ ለምርጫ ቅስቀሳ ተፍ ተፍ ይላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ትራምፕ መታመም አይፈልጉም፡፡ እርግጥ ነው ማንም መታመም አይፈልግም፡፡ ልዩነቱ መታመምን መቀበልና አለመቀበል ላይ ነው። ትራምፕ በተለይ በዚህ ሰዓት በፍጹም መታመም አይፈልጉም ነበር፡፡
ግድ ሆኖባቸው ነው በነጩ ቤተ መንግሥት በር ዘግተው ትዊት የሚያደርጉት፡፡
ለጊዜው ምክትላቸውን አሰማርተዋል፡፡ ምክትላቸው ከሞገደኛዋ ካማላ ሐሪስ ጋር ዛሬ ሌሊት ይፋጠጣሉ፡፡
ትራምፕ ቤት ቆልፈው ትዊት ሲያደርጉ ባይደን ከግዛት ግዛት እየሾሩ ነው፡፡ የትራምፕ መታመም ጉልበት ሰጥቷቸው ነው መሰለኝ በርትተዋል፡፡
ትራምፕ ‹እንቅልፎ-ጆ› እያሉ እንደሚሳለቁባቸው አይደሉም፡፡ ይኸው በየግዛቱ እየሄዱ የምረጡኝ ቅስቀሳውን አጧጡፈውታል፡፡
ዛሬ ተራው የምክትሎቻቸው ነው፡፡ እንደ ባይደንና ትራምፕ የማይጨቃጨቁ ምክትሎች፡፡
ትራምፕና ባይደን ከእንግዲህ ላይገናኙም ይችላሉ፡፡ ለምን ከተባለ አንደኛ ትራምፕ ታመዋል፡፡ ሁለተኛ ትራምፕ የሰው ንግግር አያስጨርሱም፡፡ ስለዚህ ደርዝ ያለው ክርክር ዘንድሮ ላይኖር ይችላል፡፡
ለዚህም ነው ወሳኙ ክርክር ዛሬ ሌሊት የሚደረገው ነው የሚባለው፡፡
ማን ያይላል? ሐሪስ ወይስ ፔንስ?
ካማላ ሐሪስና ማይክ ፔንስ ሁለቱም እሳት የላሱ ናቸው፡፡ ፔንስ እንዲያውም በ90ዎቹ የራዲዮ አቅራቢ ጋዜጠኛ ነበሩ፡፡ ንግግር ይዋጣላቸዋል፡፡ ሆኖም እንደ ብዙዎቹ የሬዲዮ ጋዜጠኞች አይደሉም፡፡
ሐሪስ ብርቱ ተሟጋች ናት፡፡ አንደኛ ጠበቃ እንደነበረች አንርሳ፡፡
ሁለተኛ በሴኔት የአውጫጪኝ ጉባኤዎች ላይ እንዴት ተርብ እንደሆነች አንርሳ፡፡ ምን ምን የሚያካክሉ ጎምቱ ፖለቲከኞችን በሴኔት ጉባኤ ጠርታ ትንፋሻቸው እስኪቆራረጥ ድረስ በጥያቄ የምትቀቅል ናት፡፡
ሐሪስ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመርያዋ ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት ለመሆን በዚህ ክርክር ያላትን አቅም ሁሉ ታወጣለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የ55 ዓመቷ የካሊፎርኒያ ሴናተርና የቀድሞዋ የሕግ ሰው ሐሪስ ተቀጣጣይ ርችት ማለት ናት፡፡
አንዴ የሚለኩሳት ጉዳይ ካገኘች ወደ ኋላ አታውቅም፡፡ ለዘረኞት የእግር እሳት ናት፡፡ ለጾታ እኩልነት ጠበቃ ናት፡፡ የሚርመጠመጥ ሰው ያበግናታል፡፡ ዘረኛ ፖለቲከኛ ያበግናታል፡፡ የጥቁሮች በደል ያንገበግባታል፡፡
አሁን ችግሩ ከፔንስ ነው፡፡ ፔንስ የሚያቀጣጥል ሰው አይደለም፡፡ እሳት ሲነድ ውሀ በባልዲ ይዞ ቀስ እያለ የሚራመድ ዓይነት ሰው ነው፡፡ አይበርደውም፣ አይሞቀው፡፡ ጥሎበት ተረጋግቶ ነው የሚያወራው፡፡ ሲናደድም ተረጋግቶ የሚናደድ ሰው ነው፡፡
ንግግሩ ከምስጋና ነው የሚጀምረው፡፡ በሕይወቱ ያደረጋቸው ንግግሮች ሁሉም የሚባረኩት አለቃውን በማመስገን ነው፡፡
‹‹በቅድሚያ ይህን እድል ለሰጡኝ፣ እንድተነፍስ ላበቁኝ ታላቁ መሪ ዶናልድ ትራምፕ….›› ያላለበት መግለጫ የለም፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ማይክ ፔንስ የፖለቲካ ትክክለኔት ያጠቃዋል፡፡ስለዚህ ለሐሪስ የሚመች ዓይነት ተከራካሪ አይደለም፡፡፡
ማይክ ፔንስ አሁን 61 ደፈነ፡፡ በጣም ሃይማኖተኛ፣ በጣም ክርስቲያን ነው፡፡ የኢንዲያና ግዛት ሰው ነው፡፡
አሁን እንዴት እሳትና ውሀ ሲከራከሩ በቲቪ እንደምናይ ነው ግራ የገባን ፡፡ ባይደንና ትራምፕን ባየ ዓይናችን፡፡
ከአለቆቻቸው የሚበልጡት ምክትሎች
እስከዛሬ በነበረው ልምድ የምክትል ፕሬዝዳንቶች ክርክር ማንንም ግድ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ለመርሀ ግብር የሚደረግ የወዳጅት ጨዋታ ማለት ነበር፡፡ ሌላው ምክንያት በዋናዎቹ ስለሚጋረድ ነው፡፡ ዘንድሮ ግን ይህ አልሆነም፡፡
ትራምፕ ባይቀበሉትም የአልጋ ቁራኛ መሆናቸው፤ ባይድንም እርጅና መጣና ድቅን አለ ፊቴ የሚል ዜማ የሚያዜሙ ዓይነት ሰው መሆናቸው የአሜሪካ ሕዝብ ምን ያህል ሽማግሌ ፕሬዝዳንቶች እንዳሉት ይበልጥ የሚረዳው ነገ ሐሙስ ነው ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአሜሪካ ታሪክ እንደዚህ ሁለት ሽማግሌ ፕሬዝዳንቶች ለክርክር ቀርበው አያውቁም፡፡ ሽማግሌ ፕሬዝዳንት ደግሞ ለሞትና ሕመም የቀረበ ማለት ነው፡፡ አንድ ሐሙስ የቀራቸው ባይባሉም…፡፡
ለዚህም ነው ምክትሉ በተጠንቀቅ መጠበቅ አለበት፡፡ ለዚህ ነው ሐሪስና ፔንስ የበለጠ ትኩረት ያገኙት፡፡
ሁለቱ የፕሬዝዳንት እጩዎች በባለፈው ማክሰኞ ተጨቃጨቁ አንጂ አልተከራከሩም፡፡
ስለዚህ ማን የትኛውን ፖሊስ እንደሚከተል አድማጭ ተመልካቹ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ነገ ሐሙስ ነው የአሜሪካ ሕዝብ መሪዎቹ ምን እንደሚከተሉ ሊመርጥ አይችልም፡፡
ትራምፕ ኮሮና ከበረታባቸው ይህ አሜሪካዊያን የሚያዩት የመጨረሻ ምርጫ ክርክር ይሆናል ማለት ነው፡፡
ክርክሩ በስንት ሰዓትና መቼ ይካሄዳል?
ክርክሩ የሚካሄደው ዛሬ ሌሊት ነው፡፡ በአሜሪካ ሰዓት አቆጣጠር 21:00-22:30 ሰዓት፡፡ በኛ ዛሬ ሌሊት ወደ 11፡00 ሰዓት አካባቢ፣ ሊነጋጋ ሲል ይጀመራል፡፡ ለአንድ ሰዓት ተኩል ሰዓት ይቆያል፡፡
ቢቢሲ እንግሊዝኛ ይህንን ክርክር በቀጥታ ያስተላልፈዋል፡፡
የሚቀሩት ክርክሮች በጥቅምት 15 በማያሚ ፍሎሪዳ የሚካሄደው ነው፡፡
የመጨረሻው ደግሞ በኦክቶበር 22 በናሽቪል፣ ቴነሲ የሚካሄደው ነው፡፡
ሁለቱም ክርክሮች የሚካሄዱት ግን የሁለቱ ሽማግሌዎች ሕይወት እስካለች ድረስ ነው፡፡ ሞት ደጅ ከቸች የሚልበት ዘመን፡፡
ሐሪስና ፔንስ ተመርምረዋል?
ትራምፕና ባይደን ባለፈው ማክሰኞ የተከራከሩ ዕለት ስህተት ተሰርቷል፡፡
ከክርክሩ በፊት ምርመራ መደረግ ነበረበት፡፡
ትራምፕ ጆ ባይደንንና የክርክር አጋፋሪውን ክሪስ ዋላስን ሊያጋቡባቸው ይችሉ ነበር፡፡ አንደኛ ብዙም አልተራራቁም፡፡ ሁለተኛ ይወራጩ ነበር፡፡ በስሜት ነበር የሚያወሩት፡፡
እስካሁን የፎክስ ጋዜጠኛ ዋላስም ሆነ የዲሞክራቱ መሪ ባይደን በተደጋጋሚ እየተመረመሩ ነው፡፡ ኮቪድ የለባቸውም፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ክርክር ኮሚሽን አዲስ ደንብ አውጥቷል፡፡ ካማላ ሐሪስና ማይክ ፔንስ በመሀከላቸው 12 ጫማ ርቀት እንዲኖር ወስኗል፡፡
ባይደንና ትራምፕ 7 ጫማ ብቻ ነበር የሚራራቁት፡፡
ማይክ ፔንስና ካማላ ሐሪስ ዙርያ የመስታወት ጋሻ ይታጠራል ተብሏል፡፡ ክርክሩ በሚደረግበት የዩታ ዩኒቨርስቲ ኪንግስበሪ አዳራሽ ከ200 ሰዎች በላይ እንዲገኝ አልተፈቀደም፡፡
ትራምፕን ያየ በኮቪድ አይቀልድም፡፡
ፔንስ ግን ይሄ በዙርያ መስታወት ጋሻ እንዲደረግ መወሰኑ ቅር አስኝቶታል፡፡
ክርክሩ እንደ ትራምፕና ባይደን ጭቅጭቅ ይሆናል?
ክርክር በባህሪው ሞቅ ሲል ደስ ይላል፡፡ ሲፋፋም ሕይወት ይኖረዋል፡፡ እንደ ትራምፕና ባይደን ጭቅጭቅ ሲሆን ግን ይዘቱን እንኳ ለማወቅ ያስቸግራል፡፡
ሐሪስና ፔንስ ከባሕሪያቸው በመነሳት የትራምፕና ባይደን ክርክር ዓይነት ሞቅታ ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
ፔንስ በ2016 እንደታየው፤ ተረጋግቶ ነጥብ ማስቆጠር የሚችል ተከራካሪ ነው፡፡ ድምጹ ከፍ አይልም፡፡ በፍጹም አይጮህም፡፡
ሂላሪና ትራምፕ በሚከራከሩበት በዚያ ዘመን ፔንስ ከቲም ኬይን ጋር ነበር የገጠመው፡፡ ትራምፕን በደንብ ተከላክሎታል፡፡ ሂላሪን አሳጥቷታል፡፡ ይህንኑ ዛሬ ማታ ይደግመዋል ተብሎ ይገመታል፡፡
ሐሪስ የክርክር ስልቷ እንደ ጠበቃ ነው፡፡ የዋዛ አይደለችም፡፡ የክርክር እጥፋቶችን ታውቃለች፡፡
ቦምብ ጥያቄዎችን መቼ እንዴት መጣል እንዳለባት በማወቅ የሚስተካከላት የለም፡፡ የአሁኑ አለቃዋን ባይደንን ከዚህ ቀደም አፈር ከድሜ አስግጣዋለች፡፡
ከዚህ ቀደም በጥቁሮች የመብት ትግል ታሪክ ላይ የነበረውን አቀም በመምዘዝ እንደ እባብ ነበር የቀጠቀጠችው፡፡ ለፔንስ ትመለሳለች ተብሎ አይጠበቅም፡፡
የምሽቱ የክርክር ዳኛ ማናት?
ዋላስ ትራምፕን ማቆም ያልቻለ ዳኛ ነበር፡፡ ትራምፕ ፊሽካ የማይሰሙ ሞገደኛ አጥቂ ነበሩ፡፡ ዋላስ ያን ምሽት ጡሩንባ ይዞ ቢገባም ትራምፕን አደብ ማዝገዛት ይችል ነበር ተብሎ አይገመትም፡፡
ዛሬ ማታ ዳኛዋ ሴት ናት፡፡ የዩኤስ ኤ ቱዴይ ጋዜጣ ጋዜጠኛ ናት፡፡ ስሟ ሱዛን ፔጅ ይባላል፡፡ የጋዜጣው የዋሺንግተን ቢሮ ኤዲተር ናት፡፡
9 ፕሬዝዳንቶችን ቃለ መጠይቅ ያደረገች ብርቱ ጋዜጠኛ ናት፡፡ የተዋጣላት ጋዜጠኛ፡፡ ዕድለኛ ናት፡፡ ቢያንስ እንደ ማይክ ዋላስ መከራዋን አታይም፡፡
ማይክ ፔንስ ኮቪድን የመከላከል ግብረ ኃይል የሚመራ ሰው ነው፡፡ ሐሪስ ይህን ነክሶ በመያዝ ለምን 200ሺህ አሜሪካዊያን ሞቱ እያለች በጥያቄ ታስጨንቀዋለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከሁለቱ አንዱ የዛሬ 4 ዓመት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መሆናቸው አይቀርም፡፡ እድሉ ሰፊ ነው፡፡
ስለዚህ ዛሬ ማታ ክርክሩን ማየቱ አይከፋም፡፡ እንኳን እኛ ትራምፕም በቲቪ ነው የሚያዩት፡፡ ያውም እንቅልፍ ካልወሰዳቸው፡፡