የአሜሪካ ምርጫ፡ ዶናልድ ትራምፕ በካማላ ሐሪስ አሜሪካዊነት ላይ ጥያቄ አነሱ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለውዝግብ የፈጠራቸው ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ በካማላ ሐሪስ ላይ ተነስተውባታል፡፡

ከሰሞኑ የዲሞክራቱ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ጆ ባይደን የውድድር አጋራቸው አድርገው የመረጧት የካሊፎርኒዋን ሴናተር ካማላ ሐሪስን መሆኑ ይታወሳል፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሴት-ጠልና ጾተኛ አስተያየቶችን በመስጠት ይታወቃሉ፡፡

የሐሪስን መመረጥ ተከትሎ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹እንቅልፋሙ ጆ ምን ነካው? አስጠሊታ ሴት እንደሆነች ነው የማውቀው…ብለው ነበር፡፡ ትራምፕ ይህን አስጠሊታ (Nasty) የሚለውን ቃል ለሚጠሏቸው ወንድ ፖለቲከኞችም ቢሆን እምብዛምም አይጠቀሙትም፤ በሴት ፖለቲከኞች ላይ ግን በተደጋጋሚ ይለጥፉታል።

ይህም ሰውየው የለየላቸው ጾተኛ መሆናቸውን ማሳያ ሆኗል።

ትናንት በነበራቸው የጋዜጣዊ መግለጫ ስለ ካማላ ሐሪስ የተጠየቁት ትራምፕ፣ ሐሪስ ለአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር መስፈርቱን እንደማታሟላ ሰምቻለሁ ብለዋል፡፡

ይህን ዘረኛ የተባለ አስተያየት ለመስጠት ያበቃቸው በኒውስዊክ ላይ አንድ የሕግ አዋቂ ወ/ሮ ሐሪስ ከስደተኛ ቤተሰብ መወለዷን በማስታወስ ለፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ተሳትፎ ሕጉ አይፈቅድላትም የሚል ይዘት ያለው አስተያየት መጻፋቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ሐሪስ የተወለደችው ከጃማይካዊ አባትና ከሕንዳዊት እናት በኦክላንድ፣ ካሊፎርኒያ በጥቅምት 20፣ 1964 ዓ. ም ነበር፤ እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ አቆጣጠር፡፡

ወግ አጥባቂው የሕግ ፕሮፌሰር ግን ምንም እንኳ ካማላ ሐሪስ በአሜሪካ ብትወለድም ወላጆቿ በዚያን ጊዜ በተማሪ ቪዛ ላይ ከነበሩ ሕጉ ለምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዳትሳተፍ ይከለክላታል የሚል ጭብጥ ያለው ሐሳብ አንጸባርቀዋል፡፡

ይህን በኒውስዊክ መጽሔት የታተመውን የወግ አጥባቂውን ፕሮፌሰር ሐሳብ ዶናልድ ትራምፕ ‹‹እጹብ ድንቅ›› ሲሉ አሞካሽተውታል፡፡

‹‹…በነገራችሁ ላይ ይሄ ፕሮፌሰር ቀላል ሰው እንዳይመስላችሁ፤ ሕግን ጠንቅቆ የሚያውቅና የብሩሕ አእምሮ ባለቤት ነው›› ብለዋል ትራምፕ፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የትወልድ አገር ዙርያ እንዲሁ ሐሰት ሲነዙ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ኦባማ የተወለደው ኬንያ እንጂ አሜሪካ አይደለም፤ አሜሪካ በኬንያዊ ፕሬዝዳንት እየተመራች ነው ይሉ ነበር ድሮ፡፡

ጋዜጠኞች በዚህ የሕግ ፕሮፌሰር ጽሑፍ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቋቸው ዶናልድ ትራምፕ፣ ፕሮፌሰሩን ካዳነቁ በኋላ"…እየተባለ ያለው እኮ ሐሪስ በአሜሪካ ምድር አልተወለደችም ነው፤ ፕሮፌሰሩም ይህንኑ ነው የጻፈው›› ብለዋል፡፡

ጥያቄውን ያነሳላቸው ጋዜጠኛ ቀበል አድርጎ ‹‹ ክቡር ፕሬዝዳንት፣ የሕግ ፕሮፌሰሩ እኮ ካማላ ሐሪስ አሜሪካ አልተወለደችም አላሉም፡፡ ፕሮፌሰሩ ያሉት ቤተሰቦቿ እሷን ሲወልዱ ሕጋዊ የመኖርያ ፍቃድ አልነበራቸው ከነበረ ነው…›› በማለት ፕሬዝዳንቱን እዚያው መድረክ ላይ ኩም አድርጓቸዋል፡፡

ይህንን አወዛጋቢ አስተያየት በኒውስዊክ ላይ ያሳተሙት የሕግ ፕሮፌሰር ኢስትማን ይባላሉ፡፡ በጠርዘኛና ወግ አጥባቂ አቋማቸውም ይታወቃሉ፡፡

የሰውየው ሐሳብ በሌሎች የሕግ አዋቂዎች እንዴት ይታይ ይሆን?

የበርክሌይ ዩኒቨርስቲ የሕግ ምሁርና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አዋቂ ኤርዊን ኬመረንስኪ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ የትራምፕም ሆነ የፕሮፌሰሩ በሐሪስ ዙርያ ያነሱት ሐሳብ ‹‹ውሃ የማይቋጥር›› ብለውታል፡፡

‹‹እንዲያውም ወላጆቿ በስደተኛ ቪዛ ነበሩ ወይስ አልነበሩም፣ የመኖርያ ፍቃድ ነበራቸው ወይስ አልነበራቸውም የሚለው ሁሉ ግልብና ተያያዥነት የሌለው ነጥብ ነው፡፡ ሐሪስ በአሜሪካ ምድር ስለተወለደች አሜሪካዊ ዜጋ ናት፤ አለቀ ደቀቀ።›› ብለዋል የበርክሌይ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር፡፡

እርሳቸው ለዚህ መከራከርያቸው ያነሱት በአሜሪካ ሕገ መንግሥት 14ኛው አሜንድመንት፣ አንቀጽ አንድ ላይ የተጻፈውን ነው፡፡ ‹‹ማንኛውም ሰው በአሜሪካ ምድር ከተወለደ አሜሪካዊ ዜጋ ነው፡፡

በሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ የሕገ መንግሥት መምህርና ተንታኝ ላውረንስ ትራይብ የትራምፕን በሐሪስ የትውልድ ቦታ ላይ ያነሱትን ነጥብ ‹‹ጅላ ጅል›› ብለውታል፡፡

በመጪው ኅዳር አሜሪካዊያን ፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ እያሟሟቁ ነው፡፡

ጆ ባይደን ምርጫው ከቀናቸው ወ/ሮ ከመላ ሐሪስ በዚያች አገር ታሪክ የመጀመርያዋ ጥቁር እስያዊ ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡