ኢራን የጄነራል ሱለይማኒን ደም ለመበቀል የአሜሪካ አምባሳደርን ለመግደል እያሴረች ነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ማንኛውንም የአሜሪካ ዲፕሎማት ከገደለች አይቀጡ ቅጣት እቀጣታለሁ ሲሉ ዛቱ፡፡
ይህን ያሉት ኢራን በደቡብ አፍሪካ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑትን ላና ማርክስን ለመግደል ኢራን እያሴረች ነው የሚል መረጃ መውጣቱን ተከትሎ ነው፡፡
ኢራን በማንኛውም መንገድ በየትኛውም የአሜሪካ ዲፕሎማት ላይ ጥቃት ከፈጸመች "የእጇን እንሰጣታለን" ያሉት ትራምፕ" ቅጣቱ ደግሞ የድርጊቷን 1ሺ እጥፍ የሚበልጥ ይሆናልም" ብለዋል፡፡
ይህን ያሉት ሰኞ በትዊተር ሰሌዳቸው በጻፉት ማስታወሻ ነው፡፡
ኢራን ግድያ እያሴረች ነው የሚለውን መረጃ ይፋ ያደረገው ፖለቲኮ የተባለ ጋዜጣ ነው፡፡
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሰኢድ ካቲብዛድ የጋዜጣውን ዘገባ "ቅጥፈት" ብለውታል፡፡
የፖለቲኮ ጋዜጣ እንደሚያወሳው ኢራን በደቡብ አፍሪካ የአሜሪካ አምባሳደርን ለመግደል የመረጠችው አምባሳደሩ የዶናልድ ትራምፕ የረዥም ጊዜ ወዳጅ በመሆናቸው ነው፡፡
የግድያው ዓላማም ባለፈው ጥር በአሜሪካ የተገደለባትን የተወዳጁን ጄኔራሏን ቃሲም ሱለይማኒን ደም ለመመለስ ነው፡፡
ጄኔራል ሱለይማኒ በጥር ወር በአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን የተገደለው በባግዳድ አየር መንገድ አውሮፕላን ሊሳፈር በነበረበት ቅጽበት ነበር፡፡












