ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቱርክ፡ በምሽት መዝናኛ ስፍራ ጥቃት ያደረሰው ከ1ሺህ ዓመት በላይ ተፈረደበት
የቱርክ ፍርድ ቤት ኢስታንቡል ከተማ በሚገኝ የምሸት መዝናኛ ስፍራ ጥቃት አድርሶ ለ39 ሰዎች ሞት ምክንያት በሆነውን ግለሰብ ላይ ከ1ሺህ ዓመት በላይ እስር ፈረደበት።
የኡዝቤኪስታን ዜጋ የሆነው አብዱልካዲር ማሽሪፖቭ የተላለፈበት የፍርድ ውሳኔ ከ40 የእድሜ ልክ እስራት ጋር የሚስተካከል ነው ተብሏል።
ግለሰቡ ጥቃቱን ያደረሰው የአውሮፓውያኑ የ2017 አዲስ ዓመት መቀበያ ዋዜማ ላይ ሲሆን የፍርድ ሂደቱም ለሦስት ዓመታት ዘልቋል።
አብዱልካዲር ማሽሪፖቭ የእስላሚክ ስቴት (አይኤስ) አባል ነው ተብሏል። በምሸት መዝናኛ ስፍራው ላይ ለደረሰው ጉዳትም ጽንፈኛው ቡድን ተጠያቂ ተደርጓል።
ግለሰቡ በግድያ እና የቱርክን ሕገ-መንግሥት መተላለፍ በሚሉ ክሶች ነው ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው።
አለያስ ማማሳሪፖቭ የተባለው ሌላ ግለሰብ ደግሞ በምሽት መዝናኛ ስፍራው ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ተባባሪ ሆኗል ተብሎ በተመሳሳይ ከ1ሺህ ዓመት በላይ በእስር እንዲያሳልፍ ተበይኖበታል።
የእስላሚክ ስቴትስ አባል መሆናቸውን ያመኑ 48 ሰዎችም በእስር እንዲቀጡ የቱርክ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማስተላለፉን አናዱሉ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ጥቃቱ እንዴት ተፈጸመ?
ከሦስት ዓመት በፊት አዲስ ዓመትን ለመቀበል ሬይና ተብሎ በሚጠራው የምሽት ክበብ በመዝናናት ላይ የነበሩ ሰዎች ላይ አብዱልካዲር ማሽሪፖቭ የተባለው ግለሰብ ተኩስ ከፍቷል።
በደኅንነት ካሜራ የተቀረጹ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንደሚያሳዩት ማሽሪፖቭ አውቶማቲክ መሳሪያውን አውጥቶ ያለ ማቀረጥ ሰዎች ላይ ሲተኩስ ይታያል። መሳሪያውን መልሶ ጥይት እስኪያጎርስ ጊዜ እንዲያገኝ የእጅ ቦምብ ሰዎች ላይ ሲወረውርም ነበር ተብሏል።
ጥቃቱን አድርሶ ከስፍራው ከመሰወሩ በፊት ጉዳት ደርሶባቸው ወድቀው የሚገኙ ሰዎች መሞታቸውን ለማረጋገጥ በጥይት ሲመታ ነበር።
በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል የእስራኤል፣ የፈረንሳይ፣ የቱኒዚያ፣ የሊባኖስ፣ የሕንድ፣ የቤልጄም፣ የዮርዳኖስ እና ሳዑዲ አረቢያ ዜጎች ይገኙበታል።
ከጥቃቱ በኋላ ለሁለት ሳምንታት ተሰውሮ የቆየው ማሽሪፖቭ ከብዙ ፍለጋ በኋላ በቱርክ ፖሊስ ተይዟል።